Logo
YenetaTube
በትግራይ ክልል ዳግም ጦርነት እንዳይቀሰቀስ የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው

በትግራይ ክልል የሕወሃት አመራሮችና የፌዴራል መንግሥት በደረሱበት አለመግባባት የተፈጠረውን ውጥረት ተከትሎ፣ ዳግም ጦርነት እንዳይቀሰቀስ በአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ መታቀዱን "በትግራይ ለውጥ ፈላጊ" የተባለው ስብስብ አስታውቋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎችንና ተጽዕኖ ፈጣሪዎችን ያቀፈው ይህ ስብስብ፣ ባለፈው ቅዳሜ በክልሉ ወቅታዊ ሁኔታና መፍትሔዎች ላይ ውይይት አካሂዷል።

የለውጥ ፈላጊ ስብስቡ አባል ጋዜጠኛ ዳሞራ ያህያ፤ “በትግራይ ክልል በዳግም ጦርነት ደም መፋሰስ እንዳይፈጠርና ልዩነቶች በሰላማዊና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲፈቱ ግፊት ማድረግ ያስፈልጋል” ሲሉ ለአሐዱ ተናግረዋል።

አሁን ያለው የሕወሃት ቡድን የትግራይን ሕዝብ እንደማይወክልና በክልሉ እንደሚጀመር እየተሰጋ ያለው ጦርነት የውጭ ኃይሎች ድጋፍ እንዳለበት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብና ለኤምባሲዎች ለማሳወቅ በቀጣዮቹ ሳምንታት ሰላማዊ ሰልፉ እንደሚካሄድ ገልጸዋል።

የባይቶና ዓባይ ትግራይ ፓርቲ አባል ዶክተር ፀጋዘአብ ካሱ በበኩላቸው፤ የክልሉ ነዋሪዎች እና ወጣቱ ጦርነት እንደማይፈልግ ተናግረዋል።

ባይቶና በፌዴራል መንግሥትና በትግራይ አመራሮች መካከል ያለውን ችግር ለማቀራረብ ጥረት እያደረገ መሆኑንና መንግሥት በክልሉ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች እንዳያቋርጥ የማድረግ ሥራዎች ውጤታማ እንደሆኑለት ተናግረዋል።

ጥቂት የሥልጣን ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦች የሚፈጥሩት ውጥረት የሕዝቡ ፍላጎት አለመሆኑን ለማሳወቅ እየተሰራ እንደሆነ የተናገሩት ዶክተር ፀጋዘአብ፤ “ከፌዴራል መንግሥት ጋር መሥራት ግዴታ ነው” ብለዋል፡፡
#አሐዱ

3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.