Logo
FIDEL POST NEWS
ከ"ሐቅ ምድር" ወደ ዓለም የተላከ የሰላም እና የህዳሴ ጥሪ፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በአረበኛ ቋንቋ ያስተላለፉት የረመዳን መልዕክት

​መላው የዓለም ሙስሊም ማህበረሰብ ታላቁን የረመዳን ወር መቀበል በጀመረበት በዚህ ወቅት፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለመላው የሀገሪቱ ሙስሊሞች እና በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ የእምነቱ ተከታዮች የሰላም፣ የልማት እና የታሪካዊ ትስስር መልዕክት አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ኢትዮጵያ በኢስላም ታሪክ ያላትን ስፍራ ከማውሳት ባለፈ፣ የሀገሪቱ የልማት ጉዞ ለቀጣናው ሰላም እንጂ ለስጋት እንደማይውል ገልፀዋል።

​ኢትዮጵያ፦ የፍትህ እና የታማኝነት መገኛ

​ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክታቸውን የጀመሩት የኢትዮጵያን ታሪካዊ ክብር በማውሳት ነው። ኢትዮጵያ ለኢስላም ሃይማኖት እንግዳ እንዳልሆነችና ገና በእንጭጭነቱ ወቅት ፍትህ የነገሰባት መጠጊያ ሆና ማገልገሏን ገልጸዋል።

"ኢትዮጵያ የሐቅ ምድር ናት" ያሉትን የነቢዩ መሐመድን ንግግር በመጥቀስ፣ ሀገሪቱ ከ14 ክፍለ ዘመናት በፊት ፍትህ፣ ታማኝነት እና ሰብአዊነት ድንበር እና ዜግነት እንደሌላቸው ለዓለም ያስመሰከረች ቀዳሚ ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።

​አክለውም፣ የመጀመሪያው የኢስላም አዛን አድራጊ ቢላል ኢብኑ ረባህ የኢትዮጵያ ልጅ መሆኑንና ዛሬ በዓለም ዙሪያ አምስት ጊዜ የሚሰማው ጥሪ የዚያ "ክቡር ሐበሻዊ" ድምፅ አስተጋባ መሆኑን አስታውሰዋል።

ይህ ታሪካዊ ትስስር ኢትዮጵያን ከካዕባ ጋር በልዩ መንፈሳዊ ድልድይ እንደሚያቆራኛትም አብራርተዋል።

​የልማት ጥያቄ እና የጎረቤቶች ስጋት

​በወቅታዊ የፖለቲካ እና የልማት ጉዳዮች ላይም ባሰፈሩት ፅሁፍ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ የልማት መብቷን ለማስከበር የምታደርገው ጥረት በማንም ላይ ጉዳት ለማድረስ የታለመ አለመሆኑን ገልፀዋል።

​"ከእውነት ምድር ልብ ሆነን የምናረጋግጠው፤ የልማት መብታችንን ለማረጋገጥ የምናደርገው ጥረት የሌሎችን የሕይወት መብት ለመንጠቅ አይደለም። ኢትዮጵያ ምንም ዓይነት የጂኦግራፊያዊ ስግብግብነትም ሆነ የመስፋፋት ፍላጎት የላትም" ብለዋል።
​በተለይም ስለ ታላቁ የዓባይ ወንዝ ሲናገሩ፣ ወንዙ አምላክ ለሁሉም የሰጠው "መለኮታዊ ማዕድ" መሆኑን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ የራሷን የልማት ፍላጎት ስታሟላ የሌሎችን ድርሻ የመቀነስ አላማ እንደሌላትና ዓባይ የትብብር ድልድይ እንጂ የግጭት አውድማ መሆን እንደሌለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።

"የናይል ውሃ ከእርሻችን በፊት በልባችን የሚፈስ የሕይወት የደም ስር እንዲሆን እጃችንን እንዘረጋለን" በማለት የኢትዮጵያን ቅን ልቦና ገልጸዋል።

​የባህር በር እና የቀጣናዊ ትብብር ራዕይ

​ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላትን ሀገር እየመሩ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎት "ሰላማዊ እና የህልውና አስፈላጊነት" መሆኑን ገልጸዋል። ይህ ጥያቄ የሰው ልጅ ቁጥር እድገት እና የኢኮኖሚ ፍላጎት የሚጠይቀው ህጋዊ ጥሪ መሆኑንና ይህም የጎረቤቶችን ሉዓላዊነት በማይነካ መልኩ ለጋራ ብልጽግና የቀረበ የሽርክና ጥሪ መሆኑን አስታውቀዋል። "እውነተኛ ልማት ያለው የትብብር አድማሶችን በመክፈት እንጂ የትብብር በሮችን በመዝጋት አይደለም" ሲሉ የቀጣናዊ ውህደት (Integration) አስፈላጊነትን አስረድተዋል።

​ከጦርነት ነጋሪት ወደ ሰላም ንግግር

​ሰው ልጅ በደም ቋንቋ እንደሰለቸና ጦርነት የሰውን ልጅ ትከሻ እንዳደከመ የገለጹት ዐቢይ፣ ኢትዮጵያም ከጦርነት እሳት የተማረች ሀገር በመሆኗ የሰላም ንግግር እንዲቀድም ጥሪ አቅርበዋል።

👉​ለጦርነት የሚወጣው ሀብት ለትምህርት እና ለጤና እንዲውል፤

👉​ሰውን ከመግደል ወደ ሰውን ማዳን እና ማብቃት እንዲሸጋገር አሳስበዋል።

👉​የኢትዮጵያ ህዳሴ ቁሳዊ ግንባታ ብቻ ሳይሆን፣ በመቻቻል እና በጋራ አብሮ የመኖር እሴቶች ላይ የተመሰረተ "የሥነ-ምግባር ህዳሴ" መሆኑንም አክለዋል።

​ማጠቃለያ
​ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መልዕክታቸውን ሲያጠቃልሉ፣ ኢትዮጵያ የመቻቻል ፋኖስ እና የሰላም እጅ ሆና እንደምትቀጥል ቃል ገብተዋል።

ይህ የተቀደሰ የረመዳን ወር ለልማት፣ ለብልጽግና እና ለሰላም የሚተጉ ወገኖችን ጥረት አምላክ እንዲባርክ በመለመን፣ ለመላው የእምነቱ ተከታዮች "ረመዳን ሙባረክ" ብለዋል።

​ምንጭ፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት
4 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.