Logo
SeledaPost
ገንዘብን በሀገር ውስጥ ማሳተም መጀመር ብሄራዊ ደህንነትን እንደሚያስጠብቅ ባለሙያዎች ገለጹ

በቅርቡ "የፋይናንስ እምርታ በኢትዮጵያ" በሚል በተዘጋጀው መርሃ ግብር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ ገንዘቧን በሀገር ውስጥ ማሳተም እንደምትጀምር መግለፃቸው ይታወሳል፡፡

መናኸሪያ ሬዲዮም ይህንን መነሻ በማድረግ ያነጋገራቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች፣ በሀገር ውስጥ ገንዘብ ማሳተም መጀመሩ እጅግ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸው፤ የገንዘብ (የብር) አስተዳደርንም አብሮ ማዘመን እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ክቡር ገና ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት ገንዘቧን በውጭ ሀገር ስታሳትም መቆየቷንና በዚህም ለከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወጪ ስትዳረግ መቆየቷን ጠቅሰው፤ ብርን በሀገር ውስጥ ማሳተም መጀመር ብሄራዊ ደህንነትን የሚያረጋግጥ ጭምር ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ጎረቤት ሀገራት ገንዘባቸውን ኢትዮጵያ እንድታሳትምላቸው ጥያቄ ያቀርባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅና ይህም ለሀገሪቱ ተጨማሪ ገቢ ሊያስገኝ እንደሚችል ገልጸዋል።

ገንዘባቸውን በሀገር ውስጥ በማተማቸው ውጤታማ የሆኑ ሀገራትን እንደ ምሳሌ በማንሳት፣ ኢትዮጵያ ቀደም ብላ እንደ ፓስፖርት ያሉ ሰነዶችን በሀገር ውስጥ ማሳተም መጀመሯ ለዚህ ስራ አጋዥ እንደሚሆንና ጥንቃቄ የተሞላበት የገበያ ጥናት በማድረግ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡

ሌላኛው የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ዶክተር ሞላ አለማየሁ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ገንዘቧን በሀገር ውስጥ ማሳተም መጀመሯ በመልካም የሚወሰድና ለህትመት ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚያስቀር ነው ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ ብር በሀገር ውስጥ ሲታተም ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል። በተለይም ብር ያለ አግባብ ገበያ ውስጥ እንዳይሰራጭና የዋጋ ግሽበትን እንዳያስከትል ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ይገባል ሲሉ አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡

በ"የፋይናንስ እምርታ በኢትዮጵያ" የውይይት መድረክ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባደረጉት ንግግር፤ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ብርን በሀገር ውስጥ ማሳተም የሚያስችል አቅም መፍጠሩን መግለፃቸው የሚታወስ ነው፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም፡፡ምስል - AI
9 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.