Logo
YenetaTube
ይድረስ የጎንደርን ጥምቀት ለተቻችኹ ኹሉ!
============================

ሃይማኖት ባህል እንዲሆን እንሥራ
ባህል ግን ሃይማኖት እንዳይኾን እንጠንቀቅ

አድፋጭኢዝም የዘመናችን ፈተና!!!

ጎንደር ላይ ተጨፈረ ብላችኹ እርግማን ቀረሽ ጥራዝ ነጠቅ ሂስ ስታስወነጭፉ ተመለከትን። ወቀሳውን በሁለት ከፍለን እንመልከተው። አንደኛው ወገን ከመልካም ዕሳቤ፣ ከበጎነት፣ ለሃይማኖት ከመቆርቆር ይመነጫል። መነሻ እውነት አላቸው። መዳረሻቸውን ግን ጎጠኞች፣ ጨለምተኞች፣ ቂመኞች ጠልፈውታል ብዬ አምናለሁ። ሁለተኛው ወገን ጎንደርን እና የጎንደርን ምእመናን ለማሸማቀቅ፣ ሊቃውንት የሏትም ለማሰኘት፣ ወንጌል አልተሰበከም ለማስባል፣ በሃይማኖት እና በሀገር ጭምብል ውስጥ ተወሽቀው ጎንደርን እና ኦርቶዶክሳውያንን ለማርከስ ምቹ ጊዜ ሲያደቡ የነበሩ አድፋጭ ጎጠኞች እና ወለፈንዲዎች ናቸው።

ከአሁን በፊት በዕውቀት ማነስ ምክንያት "ጴጥሮስ ሊቀ ሐዋርያ አይባልም" ብለው ለጎንደር ሊቃውንት ስልጠና ሲሰጡ የተተቹ፣ ከመድረክ ተዋርደው የወረዱ ሰበብ ፈልገው ቂም መወጣጫ ሲያደርጉ ሳይ አፈርኩ። ምክንያቱም እነሱ ተወልደንበታል ያሉበትን ቀዬ አንድም ቀን ባህላዊ ክዋኔውን ተችተው የማያውቁ ለጎንደር ሲኾን ብዕራቸውን ከአፎቱ መዘዙ፤ አፍረናል፤ ስህተት ጎጥ፣ ቀለም፣ ውፍረት እና እጥረት የላትም። የትም ቦታ ትሠራለች። በሚዛን ትከረከማለች፤ ኑረው ኑረው ከስካሩ እንደ ነቃ ሠካራም የጎንደር ሲኾን መንጋጋን ማላቀቅ ምን ይባላል? ቅናት ነው መልሱ።

ነገረ ጉዳዩን ከጎንደር እናውጣውም..... አናውጣውም

1. ቤተክርስቲያኗ ይኽ ድርጊት ዶግማዬ ነው አላለችም። ቀኖናዬ ነው ብላ አልተናገረችም። ትውፊቴ ነው ብላም አላወጀችም። ጉዳዩ የተፈጸመውም ቤተክርስቲያን ግቢ ውስጥ አይደለም። እናማ ቤተክርስቲያኗን እና ሊቃውንቷን፤ መምህራኖቿን እና ምእመናን በዚኽ ልክ መቀጥቀጥ የፍትሕ ሚዛኑን ያጎድለዋል።

2. ይኽ ነገር ጎንደር ላይ ሲደረግ የመጀመሪያ ነው ወይስ የመጨረሻ? ክንውኑ በርካታ ዓመታትን አስቆጥሯል። በዘመናዊውም በባህላዊውም። እየጠበበም እየሠፋም እዚኽ ደርሷል። ቦታውን እየቀያየረ አንዴ በቁምጣ፣ አንዴ በካሽሚር፣ ሌላ ጊዜ በጅንስ፣ እልፍ ሲል በዱላ፣ ዘለል ሲል በጎፈሬ ብቻ ዘመን ተቆጥሯል። ይኽ ከኾነ ጉዳዩ የዘንድሮውን ወቀሳ ምን አመጣው ሲባል፣ የመጀመሪያው የሕዝቡ መብዛት፣ ሲቀጥል የሚዲያ ሽፋን በማግኘቱ፣ ሢሰልስ መሐል ከተማ ላይ መኾኑ፣ አራተኛ የጎንደርን ማበብ፣ መድመቅ፣ መፍካት፣ መጉላት፣ መግነን የማይወዱ ቀን ጠባቂዎች አንዱ ጅል በለኮሰላቸው መረባረባቸው፤ ይኼ ነው ምክንያታቸው። እንጅማ በዚህ ሁለት ዓመት የጀመረ ይመስል ጎንደርን እና ኦርቶዶክሳውያንን መቀጥቀጥ ተገቢ አልነበረም።

3. ጎንደርን እና ኦርቶዶክሳውያንን እንደ መስዋዕት በግ

ፖለቲካውን መተቸት መብትህ ነው። ከፖለቲከኞች ጋርም መወቃቀስ ትችላለህ። አይመለከተኝም። በሀገር እና በሃይማኖት ስም ተደብቀህ ግን የጎንደሬዎችን እና የኦርቶዶክሳውያንን በዘመን የሸመገለ ስብእና እና ማንነት ግን ማንቆሸሽ አትችልም። ሁሉንም በሜዳው ግጠም። ለይተህ ተከራከር፣ ነጥለህ ሞግት፤ እደግመዋለሁ እኔ ፖለቲከኛ ስላልኾንኩ አይመለከተኝም። ያንን ጨዋ ሕዝብ ርኩስ፣ ራስኽን ቅዱስ አድርገኽ
ለተቀሪው ዓለም ልታሳይ ስትሞክር ግን በሰለጠነ መንገድ በገባኝ መጠን በቃል እና በመጣፍ እሞግትሃለው።

4. መርጦ ማልቀስ፤ ምን ማለት መሰለህ ኹሉም ቤት የተከሠተው ኅዘን እኩል ኾኖ ፊት እና ወንፊት እያዬህ እንባን ማንዠርዠር ማለት ነው። ወሎ ሻደይ፣ ትግራይ አሸንዳ፣ ጎጃም ጭፈራ፣ ሲዳማ፣ ወላይታ፣ ኦሮሚያ፣ ሀረር፣ ድሬ፣ ቤንሻንጉል የትኛው የኢትዮጵያ ክልል ነው ጎንደር ላይ የኾነው አይነት የሌለው? ወይም ያልተደረገው? ንገረኛ? የጎንደሩ ከሌላው የሚለዬው የሊቃውንት ሐገር መኾኑ እንዳትለኝ?! ሊቃውንቱኮ አልጨፈሩም ወዳጄ፤ ጎንደር የሃይማኖት ሀገር ስለኾነ ነው? ሌሎቹ ሃይማኖት የላቸውም እያልከኝ ነው? እንዳትሳሳት፤ ኦርቶዶክሳውያን የሌሉበት የኢትዮጵያ ክልል የለም። የቁጥር መብዛት እና ማነስ ብቻ ነው። ጎንደር ላይ ግን በኢጎ የሚሰቃዬው እና ፀረ ኦርቶዶክሱ እንደ አህያ ጆሮ እንደ ጦር ጉሮሮ ዘመቱ። ደስ የሚለው አልተሳካም አይሳካም።

በመጨረሻም እኘዚኽ ሰዎች ቁስል ባለበት አሉ። ነገረ ሥራቸው የዝንብ ነው። ወደ አበባ አይመለከቱም። ወደ ስብራት ነው የሚሮጡት። የጎንደርን ጥምቀት መልካም ጎን ለመጻፍ ብዕራቸው ደልዱም ነው። አንደበታቸው ዲዳ ነው። ምክንያቱም እነሱ ከእውነት ጋር ሳይኾን ያሉት። ከመምረጥ ጋር ነው። በተለይ ጀግና ናቸው የሚያስብላቸው ከኾነ፤ እነርሱ ኮ አይፈሩም ከተባለላቸው፤ እነሱ ኮ የቤተክርስቲያን ጠበቃ ናቸው ከተባሉ ኹሌም የሚታያቸው ስህተት ነው። 99% ደጉን ነገር ገደል ከትተው፣ በ1% ሲያላዝኑ፣ ሲወቅሱ፣ ሲከስሡ፣ ሲሳደቡ፣ ሲያንቋሽሹ ይውላሉ። ትችት፣ ስድብ፣ ማንቋሸሽ፣ ማሳነስ፣ ማራከሥ መተዳደሪያቸው ነው። ሌላ content (ይዘት ) የላቸውም። መተዳደሪያቸው ነው - አብዛኞቹ።

5. ለቅን ኦርቶዶክሳውያን ብቻ ይኽን እላለኹ፤
እናንተ ከቅንነት ነው። ለሃይማኖታችኹ ካላችኹ ቀናኢነት ነው። ለቤተክርስቲያናችኹ ከመቆርቆር የተነሣ ነው። ይኽንን እረዳለኹ። ነገር ግን እናንተ በቅንነት የጀመራችኹትን ዐሳብ እና አስተያዬት ኦርቶዶክሳውያንን፣ ጎንደርን እና የጎንደር ምእመናን ለመሳደብ ክፋታቸውን በልባቸው አዝለው ቀን ሲጠብቁ ለነበሩ መጠቀሚያ ኾናችኋል። የእናንተን ቅንነት ቅንቅን ኾነው በጥልቀት እየሠሩ ነውና፤ ኹሌም ለመተቸት እና ለመውቀስ ስንነሣ ከእኛ አስተያዬት ጀርባ እነማን ሊጠቀሙበት ይችላሉ ብላችኹ ጠይቁ፤
intension፣attention and tension የሚሉት ነገሮች ኹሌም ወቀሳ፣ ትችት፣ ሂስ፣ ስድብ ወዘተረፈ ከመስጠታችን በፊት ልናስብባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው።

በዚያ ጉዳይ ላይ ዐሳብ የሚሰጡ ሰዎችን ማንነት መመርመር መልካም ነው። የጀርባ ፍላጎት፣ በነገረ ጉዳዩ ላይ ያለቸውን ዕውቀት፣ ተገቢ ልምድ፣ የኋላ ታሪክ መፈተሽ ተገቢ ነው። ከዚያ እኛ ከሠርገኛ ጤፍ መሳይ ዐሳቦች መሐል የሚጠቅመንን መርጠን መውሰድ ያስፈልጋል።

6. በነገረ ጉዳዩ ላይ ግን እንደ ጎንደር ብቻ ሳይኾን እንደ ሀገር መነጋገር፣ መወያዬት፣ መከራከር ዐሳብ መለዋወጥ ይቻላል። ባዕዱን እያረምን፣ ማዕዱን ማቅናት ይቻላል። እኔ የምጠላው ነጥሎ መጣልን ነው፤ እኔ የምንቀው ለይቶ ማጥቃትን ነው፣ እኔ የምጸየፈው በዕውቀት የሚደረግን ፍጥጫን ሳይኾን የጩኽት ስድብን ነው። እኔ የማልወደው ዝንቡን እመታለኹ ብለኽ ግንባሩን ገንድሶ መጣልን ነው።በጨዋ ቅጥ እንወያይበት። እንደ ሀገር መፍትሔ እንፈልግበት። አለቀ። አንድን ሃይማኖት፣ አንድ ሕዝብ፣ ምእመናን ለማዋረድ የሚደረገውን ዘመቻ ግን ማንም ቆሞ አያይም።
7. እነደ ሀገር አንተ፣ አንች፣እኔ፣ እኛ ከሃይማኖታዊ ክዋኔዎች ጎን ለጎን የሚደረገውን እንደጎንደሩ ዐይነት ድርጊት እንዳይፈጸም የሠራነውን አዎንታዊ ተግባር እንጥቀስ እስቲ አለ? ቤተክርስቲያን እና ክርስቲያኖች ባሉበት በሁሉም ማኅበረሰብ ዘንድ የተቃወምነው፤ ተቃውመነው ያስተካከልነው፣ ጀምረን የጨረስነው አለ? በተነሣው ርእሰ ጉዳይ ላይ እኔ ይኽን ሠርቼ ይኽን አሳክቻለሁ እንበል እስቲ? ካለ ጻፉ። ከሌለ እንደ ሀገር ይሠራበት እንጅ ጎንደርን እና የጎንደርን ምእመናን እንዲኹም እንግዶቿን ለይቶ ማጥቃት ዋጋ እንደሚያስከፍል እንወቅ

ስንጠቀልለው ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ከባህል፣ በዓልን ከትውፊት፣ ዶግማን ከቀኖና እየለየን እና ጠንቅቀን እያወቅን ስህተቶች ሲታዩ ማሳጣት፣ ማጋነን ልታይ ልታይ በሌለበት መንፈስ፤ በሚያጸና እና በሚያቀና ፍኖት እየተጓዝን ወደ ፊት እንድንጓዝ እግዚአብሔር አምላክ ይርዳን።

ሃይማኖት ባህል እንዲሆን እንሥራ
ባህል ግን ሃይማኖት እንዳይኾን እንጠንቀቅ!!!

የማርያምወርቅ ተሻገር (መ/ር)

9 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.