Logo
FIDEL POST NEWS
​"ግሪንላንድ ወይም ሞት"፦ ትራምፕ ደሴቲቱን ለመውሰድ ቆርጠው ተነሱ

​የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግሪንላንድን በአሜሪካ ቁጥጥር ስር ለማድረግ ያላቸውን ፍላጎት በድጋሚ በማንቀሳቀስ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ቀስቅሰዋል።

ፕሬዝዳንቱ የዴንማርክ እና የግሪንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በዋይት ሃውስ ሊያደርጉት ከታቀደው ወሳኝ ስብሰባ ጥቂት ቀደም ብሎ በሰጡት መግለጫ፣ ግሪንላንድ ለአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት ወሳኝ መሆኗንና ሌላ አማራጭ ተቀባይነት እንደሌለው አስታውቀዋል።

እንደ ትራምፕ ገለጻ፣ ደሴቲቱ አሜሪካ ለምታቅደው "ጎልደን ዶም" የተሰኘ ግዙፍ የፀረ-ሚሳይል መከላከያ ስርዓት ግንባታ ስትራቴጂካዊ መሠረት ናት።

​ፕሬዝዳንቱ የግሪንላንድን የወቅቱን የመከላከያ አቅም በጽኑ የነቀፉ ሲሆን፣ "ሁለት የውሻ መንሸራተቻዎች (Dog Sleds) ለሀገር መከላከያ አይበቁም" በማለት የደሴቲቱን የጥበቃ ጥረት አጣጥለዋል።

ኔቶ በግሪንላንድ ያለውን መገኘት እንዲያጠናክር በአውሮፓውያን የቀረበውን የመፍትሄ ሃሳብ ውድቅ ያደረጉት ትራምፕ፣ አሜሪካ ደሴቲቱን ካልተቆጣጠረች ሩሲያ ወይም ቻይና ቀድመው ሊይዟት እንደሚችሉ በማስጠንቀቅ "ይህ ደግሞ በፍጹም እንዲሆን አንፈቅድም" ሲሉ በቁጣ ገልጸዋል ።

​በሌላ በኩል፣ የዴንማርክ እና የግሪንላንድ መንግስታት የአሜሪካን ጥያቄ ሙሉ በሙሉ ውድቅ አድርገውታል። የዴንማርክ ጠቅላይ ሚኒስትር ሜት ፍሬደሪክሰን አሜሪካ ዛቻዋን የምትቀጥል ከሆነ የኔቶ ጥምረት ሊፈርስ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

ዛሬ በዋይት ሃውስ በሚካሄደው ስብሰባ ላይ የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ በድንገት መገኘታቸው ደግሞ ስብሰባው በሰላማዊ ውይይት ፋንታ ወደፊት ለፊት ፍጥጫ ሊቀየር ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት በዲፕሎማቶች ዘንድ ፈጥሯል።
5 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.