Logo
FIDEL POST NEWS
ምግቦች ላይ በሚጨመሩ ኬሚካሎች ምክንያት መሀንነት እየጨመረ ነው ። የሰው ልጅ ጤና ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ አደጋ ላይ ወድቋል ተባለ

የተለያዩ የአሜሪካ እና የብሪታኒያ፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የቅድመ መከላከል ጤና ኢንስቲትዩት፣ የአካባቢ ጤና ማዕከል እና ሌሎች የበርካታ ድርጅቶች ሳይንቲስቶች በኬሚካል አጠቃቀም ላይ ጥናት አድርገዋል።

በጥናቱ መሰረት ምግቦች በፋታሌትስ፣ በቢስፌኖልስ፣ በፀረ-ተባይ መድኃኒቶች እና በፒኤፍኤኤስ 'ዘላለማዊ ኬሚካሎች' ምክንያት መርዛማ እየሆኑ መጥተዋል።

​በዓለም ዙሪያ በተለያዩ የምግብ ምርትና ማቀነባበሪያ ሂደቶች ውስጥ የተለያዩ ዓይነት ኬሚካሎች ጥቅም ላይ ይውላሉ። እነዚህ ኬሚካሎች ለሰው ልጅ ጤና እና ለዓለም አቀፍ የእርሻ ስርዓት ትልቅ ስጋት እየሆኑ ነው።

ካንሰርን፣ የነርቭ ልማት መጎዳትን፣ ከመጠን ያለፈ ውፍረትን እና የስኳር በሽታን ሊያስከትሉ ይችላሉ። ከዚህም በላይ እነዚህ ኬሚካሎች የሆርሞን መዛባት ችግሮችን፣ በተለይም መሀንነትን እያስከተሉ ነው።

​በኬሚካል አጠቃቀም ምክንያት የሚከሰቱ የጤና አደጋዎች እና የበሽታ ወጪዎች በዓመት እስከ 2.2 ትሪሊዮን የአሜሪካን ዶላር ሊደርሱ ይችላሉ።

በተጨማሪም በ21ኛው ክፍለ ዘመን ዓለም አቀፉ የውልደት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል።

ጥናቱ የተካሄደው ለተባበሩት መንግስታት የዘላቂ ልማት ግቦችን እና የፓሪስ የአየር ንብረት ስምምነትን ተግባራዊ ለማድረግ በሚሠራው ሲስተሚክ (Systemic) የተባለ ድርጅት ዋና የምርምር ቡድን መሪነት ነው። የምርምሩ ውጤት ረቡዕ ዕለት ይፋ ሆኗል ሲል ዘ ጋርዲያን አስነብቧል ።

​በታተመው ሪፖርት መሰረት፣ የዓለም ምግብ በፋታሌትስ (ፕላስቲኮችን ለስላሳ፣ ተለዋዋጭ እና ዘላቂ ለማድረግ እንዲሁም ምግብን ለማሸግ የሚያገለግሉ ኬሚካሎች)፣ በቢስፌኖልስ (ፕላስቲኮችና ሙጫዎችን ለማምረት የሚያገለግል ቁልፍ ኬሚካል)፣ በፀረ-ተባይ መድኃኒቶች (በእርሻ ውስጥ ነፍሳትን፣ አረሞችን እና በሽታዎችን ለመቆጣጠር የሚያገለግሉ ኬሚካሎች) እና በፒኤፍኤኤስ 'ዘላለማዊ ኬሚካሎች' እየተመረዘ ነው።

​ሪፖርቱ የእነዚህ ኬሚካሎች የአሁኑ የአጠቃቀም ደረጃ በዓለም ዙሪያ ከቀጠለ፣ በ2025 እና በ2100 መካከል ከ200 ሚሊዮን እስከ 700 ሚሊዮን ያነሱ ሕፃናት ይወለዳሉ።

ጥናቱ እንደሚያመለክተው እነዚህ ኬሚካሎች በሽታን ከማስከተል ባሻገር በአካባቢው እና በእርሻ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ ነው።

የፒኤፍኤኤስ እና የፀረ-ተባይ መድኃኒቶች ተጨማሪ ወጪዎች በተጎዳ የእርሻ ምርት እና የውሃ ደህንነት ምክንያት ተጨማሪ 640 ቢሊዮን ዶላር ሊደርሱ ይችላሉ።

​ ጥናቱ እንደሚለው፣ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ዓለም አቀፍ የኬሚካል ምርት 200 እጥፍ ጨምሯል፣ በአሁኑ ጊዜ ከ3.5 ሚሊዮን በላይ ሰው ሠራሽ ኬሚካሎች በገበያ ላይ ይገኛሉ።

ከእነዚህ ውስጥ ስለ አደጋቸው በቂ መረጃ የሚታወቀው ጥቂቶቹ ብቻ ሲሆኑ፣ የቀሪዎቹ ተጽእኖዎች እስካሁን አልታወቁም። ዓለም አቀፍ የህፃናት ጤና ባለሙያ እና የሪፖርቱ አቅራቢ ከሆኑት አንዱ የሆኑት ዶ/ር ፊሊፕ ላንድሪጋን ሁኔታውን 'የመንቂያ ደውል' ሲሉ ጠርተውታል።

"ዓለም በኬሚካል ብክለት ላይ እርምጃ መውሰድ አለባት። ይህ እንደ አየር ንብረት ለውጥ ትልቅ ስጋት ነው" ብለዋል። "እነዚህ ኬሚካሎች በልጆች አዕምሮ እድገት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳሉ፣ ብልህነትን፣ ፈጠራን እና የዕድሜ ልክ ምርታማነትን ይቀንሳሉ" ብለዋል።
6 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.