Logo
YenetaTube
አዲሱ የሌቦች ዘዴ

ኢትዮጵያ ውስጥ የመንግስት ባለስልጣናት የሚገኙበትን ማንኛውንም ስብሰባና Event ልክ እንደመንግስት አካል ተከታትለው የሚሳተፉ የመንግስት ሰዎች ነን የሚሉ ግን ምንም ውስጥ የሌሉ ግለሰቦች በዝተዋል። አላማቸው በቦታው ከሚገኙ ባለስልጣናት ጋር ፎቶ በመነሳት ከመንግስት ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ለህዝቡ ማሳየት ነው።

ሰሞኑን እየሰማሁ ያለሁት ነገር ይገርማል። የዘመኑ አጭበርባሪዎች ፋሽን የመንግስት ሰዎችን ስለማውቅ ጉዳይህን ልግደልልህ የሚል ሆኗል። ከተማው ላይ ሁሉም ቦታ የምታገኟቸው ግለሰቦች፣ በማይመለከታቸው ስብሰባና መድረክ ዘንጠው ከፊት የሚቀመጡ ሰዎች፣ ባለሃብት ነን ብለው ሚዲያ ላይ በማጮህና የመንግስት ባለስልጣናትን በማስጨነቅ አብረዋቸው ምሳ በመብላትና ፎቶ በመነሳት ከነሱ ጋር የተለየ ግንኙነት እንዳላቸው በማስመሰል ራሳቸውን አድራጊ ፈጣሪ አድርገው በህዝብ ጭንቅላት ውስጥ በመሳል ሰዎችን "ይህንን ጉዳይ ላስፈፅምላችሁ፣ እገሌ ከሚባለው ባለስልጣን ጋር ላስተዋውቃችሁ" በማለት በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ የሚዘርፉ ብዙ ሰዎችን እያየን ነው። ተደርሶባቸውም በቅርቡ የታሰሩ አሉ።

በዚህ ብቻ አይበቃም። እነዚህ ሰዎች መንግስትን የሚደግፉ መስለው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ወይም ክብርት ከንቲባዋን ብቻ በመነጠል ለሰው ልጅ የማይቀርብ ሙገሳና ከንቱ ውዳሴ ሲደረድሩ በመዋል፣ ከባለሃብቶች ጉዳይ እናስፈፅምላችሁ፣ ሚኒስትር እገሌ በግል ያናግረኛል፣ የእንትን ሚኒስትሩ ጓደኛዬ ነው በማለት መንግስት ላይ እንደተውሳክ ተጣብቀው የግል ፍላጎታቸውን የሚያካሂዱ ብዙዎችን እያየን ነው።

በደምብ እስከማውቀው ድረስ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ ሌሎቹ አመራሮች ከንቱ ውዳሴና አምልኮ ቀረሽ ሙገሳን አብዝተው የሚጠየፉ ናቸው። መሪን ማክበርና መንግስትን መደገፍ ልክና ስርአት አለው ከዚያ ባለፈ ግን መስመር የዘለለ ማሽቃበጥ በመጀመሪያ ደረጃ ራሳቸው መሪዎቹን ምቾት ይነሳል ሲቀጥል ደግሞ ከልብ ያልሆነ ውዳሴ ስለሆነ የውሸት ነው። አሁን ኩላሊቱ እጅግ ጤነኛ ለሆነ መሪ ከመሬት ተነስተው "አስፈላጊ ከሆነ ለአብቹ የአካል ክፍሌን ቆርጬ እሰጣለሁ" የሚሉ ሰዎች ችግር ቢፈጠር ፍሬቻ ሳያበሩ የሚታጠፉ አጭበርባሪዎች ናቸው። ከዚህ ባለፈ እንዲህ አይነት መስመር የዘለለ ከንቱ ውዳሴ ሐገሪቱ በአንድ ግለሰብ ብቻ የምትመራ አድርጎ ከመሳል ያለፈ አንዳች ፖለቲካዊ ትርፍ የለውም። እንደነዚህ አይነት ሰዎች ለመንግስት ጠላት ከመፈብረክና ሐገረ መንግስቱን በተለየ መልክ ከመሳል ያለፈ አንዳች ጥቅም የላቸውም።

በዚህ አመት ፖሊስ እየወሰደ ያለው እርምጃ የመንግስትን አቋም በደምብ ያሳያችሁ ይመስለኛል። ባለሃብት ነኝ ብለህ በየሄድክበት የመንግስት ደጋፊነትህን ስለተናገርክ በወንጀል ከመጠየቅ አታመልጥም። መንግስትን እደግፋለሁ ብለህ በብሔር ውስጥ በመሸሸግ ህዝብና ህዝብን ስታባላ ከተገኘህ ብልፅግናን ከመደገፍ አልፈህ ብታመልከውም ትታሰራለህ። (ዳለቻን አስታውስ) የመከላከያን ልብስ ለብሰህ መሬት እስኪጠብህ ብትንጎማለል፣ ቀን ከሌት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ስም እያወደስክ ብትውል፣ ከፈለከው ሚኒስትርና ከፍተኛ ባለስልጣን ጋር ምሳ የምትበላ ሰው ብትሆን፣ በመንግስት ደጋፊነት ስም ምስኪኑ ህዝብ ላይ የፈለኩትን የማድረግ ልዩ ፍቃድ አለኝ ያልክ ቀን ራስህን እስር ቤት ታገኘዋለህ። በኢትዮጵያ ምድር ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል ነው።

እዚህ ጋር ሳልናገር የማላልፈው በተለይ ባለሃብቶች እገሌ ከመንግስት ጋር ግንኙነት አለው በማለት ሚዲያ ላይ ከአስሩ ባለስልጣን ጋር እየተለጠፈ ፎቶ ለተነሳ ሁሉ አታሸርግዱ። እኔ ያለኝ መብት፣ አንድ ባለስልጣን ያለው መብት፣ አንድ ደሃ ያለው መብት፣ በኢትዮጵያ ሰማይ ስር እኩል ነው። እኩልም ሊሆን ይገባል። የራሱን ፎቶ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር እያቀናበረ የቤተመንግስት ባለሟል እንደሆነ የሚያስመስል ቀጣፊ የመንግስት ደጋፊ ነኝ ባይ አንዳች የሚፈይድላችሁ ነገር የለም። አብዛኞቹ መሬት ጠበበን የሚሉ ሰዎችን እላይ ያሉ ሰዎች ከነመፈጠራቸውም አያውቋቸውም።

እኔን ጨምሮ ከመንግስት ጋር የተለየ ግንኙነት ያለን የሚመስሏችሁ ሰዎች ከየትኛውም ባለስልጣንና የጦር መሪ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለን ልነግራችሁ እፈልጋለሁ። አትሞኙ። መብታችሁ የሆነን ጉዳይ በህጋዊና በህጋዊ መንገድ ብቻ ሄዳችሁ ጨርሱ። ምንም ያህል መንገዱ ከባድ ቢሆን መብታችሁን ለሆነ ግለሰብ አሳልፋችሀየ አትስጡ። ከዚህ ውጪ ለመንግስት የበኩር ልጅ ነን በሚሉ ሰዎች ሃብት ንበረታችሁን እንዳታጡ እመክራችኋለሁ። ሌሎቻችሁም አደብ ግዙ። ዶክተር አብይን እንደምትሉት ከልብ የምትወዱ ከሆነ ሃላፊነት የሚሰማው ዜጋ ሁኑለት። እነዚህ እይታዎቼ ላለፉት 3 አመታት ኢትዮጵያ በብዛት ስመላለስ የታዘብኳቸው እና ያየኃቸው እውነታዎች ናቸው::

Via natnael mekonnen

6 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.