Logo
Getu Temesgen
ታላቁ ተዋናይ ኪሮስ ኃ/ስላሴ በሰይፉ ሾው ፦

በዘሪሁን ተዝናኑ

★ የዛሬ 10 ዓመት ነው እንደድንገት አይኔ ብዥ ያለብኝ።

★በነገራችን ላይ ዕድሜዬ 70 ሞልቷል።

★ ከሐረር አንድ አይነስውር ደውሎ እንኳን ወደእኛ ክለብ መጣህ ያለኝ አለ።

★ ህይወት ለማንኛችንም ዋስትና አልገባችም።
በአደጋም ሆነ በጤና ማጣት ጠግቦ በመሰበርም ከነሙሉ
አካላችን ላንቀበር እንችላለን።

★ ሙሉ ነገር የነበረን ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች የአካል
ጉዳት ሊያጋጥመን ይችላል።

★ ሰይፍሻ አንተም ፀጉር ጎሎሃል ስለዚህ አካል ጉዳተኛ ነህ።

★ የኔ በሽታ ግላኮማ ነው። ግላኮማ ዓይንን የማጥቃት ዕድሉ ከፍተኛ ነው። ከስኳር በሽታ ጋር ተያያዥነት ያለው ነው።

★ የዓይን ብርሃን ማጣት የምታውቀውን ሰውና ከተማ ታጣበታለህ።

★ ሀገሬን ከናቅፋ እስከ ሞያሌ ፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ ፣
ከምስራቅ እስከምዕራብ ያላየሁት ሀገር የለም።

★ ንባብ ማለት ከዓይን ጋር ኮንታክት መፍጠር ማለት ነው።

★ ኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል ጓደኛዬ ልጁን ድሮ በዓይኔ
ማየት ባለመቻሌ አልቅሻለሁ።

★ ልጆቼ ሲያገቡም ቬሎዋቸውን አላየሁም። ደስታቸውን
በዓይኔ አላየሁም። ሁለቱንም ሴት ልጆቼን በአንድ ቀን ነው
የዳርኳቸው።

★ አንደኛዋ ልጄ ስትወልድ ልጇን መልኩን አላየሁትም።
በዳበሳ ብቻ ነው። ግን እንዳየሁት ነው የምቆጥረው።

★ መጋቢት 17/2017 70ኛ ዓመቴን አስመልክቶ ተስፋ ኢንተርፕራይዝ ከልጆቼ ጋር አከበረልኝ።

★ ከዩኒቨርሲቲ እንደወጣሁ ፦ ጠልፎ በኪሴ ፣ የቬኑሱ ነጋዴ እና ንጉስ ሊርን ከደበበ እሸቱ ጋር ተውኛለሁ።

★ ከኔ ሲኒየሮች ጌትነት እንየውንና ተፈሪ አለሙን አደንቃለሁ።
እነሱ እያሉ ለምን እኔ እሸለማለሁ እላለሁ። ራሱን የሚደብቀውም አስታጥቃቸው ይሁንም እንደዛው።

★ተዋናይ ግርማ መኮንን መስከረም 7/1983 የሞተ የኛ ታላቅ መምህር ነው። ኮሜዲ ብትለው ፣ ትራጄዲ ብትለው ፣
ፋርስ ብትለው የማይችለው አይነት የትወና ስታይል የለም።
የሚተካው ሰው የለም። እኔ ነኝ ምርጥ ተዋናይ የሚለውን ሁሉ የሚያስንቅ ነበር። ይኼ ሰው በአጭር ተቀጨ።
ዕድለኛ ሆኜ አብሬው የመስራት ዕድሉን አግኝቻለሁ።

★ ከዩኒቨርሲቲ ወጥቼ ቴአትር መስራት ከጀመርኩኝ
42 ዓመት ሆኖኛል።

★ የአይነ ስውር ገፀ - ባህሪ ፈጥሮ ሊያጫውተኝ የሞከረ የለም።

★ ዳና ድራማ ላይ አይኔ እየደከመ እያነበቡልኝ አክት አድርጊያለሁ።

★ አደይ ድራማ ላይ ለአንድ ዓመት ከሁለት ወር ያህል
እየተነበበልኝ ተውኛለሁ።

★ ማንያዘዋል እንደሻው የተረጎመውን የመጨረሻው ፍርድ
የተሰኘውን ቴአትር እየተለማመድነው ነው። ታህሣሥ 9
ለዕይታ ይበቃል።

★ ጡረታ ወጥቼም ሀገር ፍቅር ከሠራተኛው እኩል ነው
የምገኘው።

★ ሰው በትዝታ ነው የሚኖረው። ወጣት ስትሆን ነው
በተስፋ የምትኖረው።

★ ፊልማችን በተለያየ ቋንቋ ቢሰራ ከዓለም ጋር የተሻለ
እንተዋወቃለን።

★ በ14 ዓመቴ ነው ሲጋራ ማጨስ የጀመርኩት። ልጆቼ ግን በአካል ሳጨስ አይተውኝ አያውቁም። ሲበቃኝ ግን በቃኝ።
አንድ ፓኬት መቶ ብር ሲገባ አቆምኩኝ። በቀን አንድ ፓኬት
ከግማሽ ነበር የማጨሰው።
አንድ ትልቅ ቪላ ቤት የሚገዛ ብር በዓመት በሲጋራ አጠፋ ነበር። እኛ እንደምናደርገው በዚህ ዘመን ወጣት በአደባባይ ሲያጨስ አላየሁም።

★ የዛሬ ወር ብሬል ተምሬ የመጀመሪያውን ሰርተፍኬት
ወስጃለሁ።

★ በህይወቴ የማልረሳው የመድረክ ገጠመኝ ፦
ጊዜው 1977 ዓ.ም እኔ ተፈሪ እና ደበበ መድረክ እየመራን
በላይነሽ ውባንተ የተሰኘች ዘፋኝ ፦
ምን አስገለበጠኝ ወተቱን በጋን
ችዬ እገፋዋለሁ የማልለውን
የማልለውን የሚለውን ሳትጨርስ መድረክ ላይ ወደቀች።
ወደ ሆስፒታልም ተወሰደች።
የተሾመ አሰግድን ስንብት ዘፈን
ይህች አጋጣሚ በአንድ አገናኝታን
የፍቅርን ሸማ ደርባ አጎናፅፋን
ሆኖም ሳናስበው ጊዜው በመሆኑ
በቃ ተለያየን መሪር ነው ሀዘኑ
በኋላ ስንሰማ ሆስፒታል የሄደችው ዘፋኟ ሞተች ተባለ።
በነጋታው ለቀብር ያ ሁሉ ተመልካች ተገልብጦ መጣ።
ከዛ በኋላ ስንብት የተሰኘውን ዘፈን ስሰማ ዘፋኟ ከአዕምሮዬ አትጠፋም።

በመጨረሻም ፦ ልበ - ብርዓኖቹ ታዳጊዎቹ አይነስውሮቹ እህትማማቾች ፦ ሄራንና ሶልያና ለአርቲስት ኪሮስ ኃ/ስላሴ
በብሬል የተፃፈ የመፅሐፍ ቅዱስ ጥቅስ አበርክተውለታል።

እግዚአብሔር መድሃኒቴ ነው
የሚያስደነግጠኝ የሚያስፈራኝ ማነው
>
ኪሮስ እንወድሃለን ! እናከብርሃለን !
ዕድሜ ከጤና ይስጥልን !
" ሄራንና ሶልያና " ❤❤❤❤❤

" እግዚአብሔር ለትልቅ ደረጃ ያብቃችሁ። "
>

አርቲስት ኪሮስ ኃ/ስላሴ ፦ ለሰጠኸን የኪነጥበብ ስራዎችና
ወደፊትም ለምትሰጠን ጥበባዊ ስራዎች እናመሰግናለን።
ፈጣሪ ዕድሜና ጤና ይስጥህ !
አክባሪህና አድናቂህ

ዘሪሁን ተዝናኑ

ሞቅ ካለ የሚነበብ ፊርማ ጋር !!!

6 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.