Logo
Getu Temesgen
የኛ ዲዮጋን : ዶ/ር ጴሌ ዳሮታ ...
____________

(ፍልስፍናን ከነነፃነቷ የኖራት፣ በልዩ ትወና የሰበካት አይረሴ ምሁር!)
#ethiopia | የዕውቁን የፍልስፍና መምህራችንን የዶ/ር ጴሌ ዳሮታን ህልፈት ሰማሁ። ከልብ አዝኜያለሁ።

በእርግጥ ፔሌ ቀጥታ የእኔ አስተማሪ ሆኖ ባያውቅም፣ ዝናውን በመስማት ጉዱን ለማየት ከጓደኞቼ ጋር ከአንድም ሁለት ቀን በእርሱ ሌክቸር ክፍለጊዜ ገብቼ ሎጂክን እንደ መደሰቻ ሽቶ ተርከፍክፌ ነው የወጣሁት ብል ማጋነን አይደለም!

ጴሌ በጣም ቀልደኛ ሰው ነበረ። ስሙን በእንግሊዝኛ "Pelle" ብሎ ይፅፍና፣ ዕድሜ ለእንግሊዝኛ "ጴ" የሚል ፊደል ስለሌለው ስሜን ከጴሌ ወደ ፔሌ ቀየረልኝ — በማለት ያሳቀንን አልረሳውም!

አንዴ መምህር ፔሌ በፍልስፍና (ሎጂክ) ክላሱ በሆነ ርዕስ ሰበብ አንስቶ አንድ ጥያቄ ጠየቀ ተማሪዎችን። እስቲ መጀመሪያ ሴቶች መልሱልኝ አለና ጠየቀ፦

"እዚህ ካምፓስ የምታውቂው አንድ ልጅ
ወዳንቺ መጥቶ፣ አፈቅርሻለሁ እሺ በዪኝ፣
አለበለዚያ በዚህ ገመድ ነው የምታነቀው
ቢልሽ፣ ምን ትመልሺለታለሽ?"

እጁን አንስቶ የሚመልስ ጠፋ። ሁሉም ዝም አለ። ከዚያ ፔሌ ራሱ በድንገት ዓይኑ የገባችውን እመቤት የተባለችውን (ኋላ ሎውስኩል አብረን የገባን የነጌሌ ልጅ) ጠየቃት።

መጀመሪያ "እኔ እንጃ? ምን እንደምመልስለት አላውቅም" አለች። ጴሌ በጣም ተበሳጨ። እንዴት እኔእንጃ ትያለሽ? ፈትሽ ገመዱን እያየሽ? ብሎ ደግሞ ጠየቃት። ተማሪዎች ሳቅን።

እሷ ግን "እኔ ካላፈቀርኩት እሱ ስላፈቀረኝ ብቻ እሺ ልለው አልችልም!" የሚል ቆፍጣና አቋሟን ደገመችለት። ተማሪው በመልሷ ሳቀ። በእርግጥም አቋሟ ነው፣ መብቷም ነበር!

ጴሌ ግን ይበልጥ በተበሳጨ አኳኋን የእሷን ቃል እያሾፈ ደገመው። ክፍሉ በሣቅ ፈረሰ። በመጨረሻም ፔሌ፦

"አንድ የመጨረሻ ዕድል እሰጥሻለሁ፣
ልጁ እምቢ ካልሽው በቀጥታ በገመድ
ራሱን እንደሚሰቅል በእርግጠኝነት ብታውቂስ?
መልስሽ የተለየ ይሆን ነበር?"

አላት። ልጂት ግን ድርቅ ብላ ቀረች። ትንሽም እልህ የተጋባች ትመስል ነበረ ከመምህሩ ከፔሌ ጋር።

"ኖ እኔ እስካላፈቀርኩት የፈለገውን ቢያደርግ
እሺ አልለውም፣ ባያደርገው ደስ ይለኛል፣ ግን
ሞንም ማድረግ አልችልም...!"

ፔሌ ሁለት እጆቹን የተመለጠ ጭንቅላቱ ላይ አድርጎ ሌክቸር አዳራሹ ውስጥ "ኡኡኡኡ....!!" ብሎ ጮኸ። ተማሪው በሙሉ በሣቅ ተንከተከተ። እሱ ግን ጮኾ አላበቃም!

"ውጪ ከዚህ አንቺ ጨካኝ!?
ከፈለገ ይሰቀል፣ ካላፈቀርኩት አያገባኝም..
ይባላል? አረመኔ! የሰው ነፍስ ምንም
የማይመስልሽ ጨካኝ ውጪልኝ አሁን...!!"

ልጅቷ ደነገጠች። ሁላችንም ቀልዱንም መስሎን ነበር። ፔሌ ግን "ውጪ እኮ ነው የምልሽ!" ብሎ ደገመላት።

ጥቂት ለመከራከር ሞከረች፦

"እንዴ? ምን አደረግኩ? ጠየቅከኝ፣ መለስኩኝ...!"

አላስጨረሳትም። በደረጃዎች እንደ ስቴዲየም በተደረደሩት ወንበሮች ሽቅብ በደረጃዎቹ ወጥቶ፣ ልጂቱን ጎትቶ አስነሳትና አስወጣት! ስትወጣ ክፍሉ በአንድ እግሩ ቆመ።😀🤪😌 በጭብጨባና በወከባ፣ በወጣቶች ሣቅ!!

ከወጣች በኋላም አላቆመም ነበረ ፔሌ፦

"ይህቺ ጨካኝ! ይሙት በቃ ምናገባኝ
ብላ የምትፈርድ!? አረመኔ! ለሰው ህይወት
ምንም ዋጋ የሌላት! ግፈኛ! የታባቷ የእጇን
ነው የሰጠኋት...!!"🤪😀

ተማሪው በሣቅ አበደ አይገልፀውም! አሁን ይህ ከሆነ በትክክል ወደ 28 ዓመት ሆነው መሠለኝ! ጊዜው ይበርራል! ይገርማል።

ግን ያቺን ፔሌ እመቤትን ከክፍሉ ጎትቶ ያባረረባትን ቀን ሁሌም በህይወቴ ሳስስታውሳት የምትኖር ገጠመኝ ነች። ፔሌ ምናልባት የህይወትን ክቡር ዋጋ በእኛ በተማሪዎች አዕምሮ ውስጥ... በቃላት ቀምሮ በመንገር ብቻ እንዳንረሳው አድርጎ መከተብ እንደማይችል ተረድቶ ይሆናል ብዬ አስባለሁ አሁን ላይ!

መምህር ፔሌ ነገሮችን dramatize አድርጎ እንዳትረሳው አድርጎ በትውስታህ የሚያትምባቸው እንዲህ የመሠሉ በርከት ያሉ ድንገታዊ ትዕይንቶች ነበሩት!

ፍልስፍና ሲባል ራሱ እንደሆነ የዕብደት ዓይነት አድርገን ለምንቆጥር ሰዎች የፔሌ አስቂኝ፣ ሊገመት የማይችል፣ አጓጊና መሳጭ ክላሶች በብዙ ተማሪዎች ዘንድ ስሙን እጅግ ተወዳጅና ዝነኛ አድርገውት የቀሩ ይመስለኛል!

ወደ ካምፓሱ የመጣ አዲስ ባች ሁሉ... "ፔሌ ነው ፊሎሶፊ አስተማሪህ? እሱንማ ማየት አለብህ...!" እየተባለ በሲኒየሮች ለፍሬሾች ዝናው የሚነገርለት...፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በወቅቱ ከነበሩ መምህራን ሁሉ ስሙና ትያትሪካል የሆኑ ንግግሮቹ እየተጋነኑ የሚወራለት፣ ሲበዛ አነጋጋሪና በጣም ተወዳጅ፣ legendary personality ነበረ!

የፍልስፍና ሌጀንዱ፣ ፔሌ ዳሮታ፣ እንደማስታውሰው በእኛ ጊዜ (1990 ዓ/ም ላይ) "ዶክተር" ተብሎ አይጠራም ነበረ። ወይ በወቅቱ ዶክትሬቱን አልሠራም ነበር፣ ወይ አይጠራበትም ነበር ማለት ነው!

ግን እውነትነቱን የማረጋገጥ ዕድሉ ባይኖረኝም፣ ያኔ ስለ ፔሌ ከምንሰማቸው ታሪኮች አንዱ፣ ፔሌ ድሮ ከፍልስፍና ትምህረት ክፍል ሲመረቅ፣ ብቻውን የተመረቀ ተማሪ ነበረ ይባላል!

በእኛ ጊዜ የፍልስፍና ትምህርት ክፍል እንዲዘጋ ተደርጎ ነበር። እና በcommon courses ውስጥ፣ወይ በየፋከልቲው ባሉ ኮርሶች ውስጥ ነበር ፍልስፍናን የምንማረው።

(በኋላ እነ ዶክተር ሣሙኤል አሰፋ ናቸው በ90ዎቹ መጨረሻ አካባቢ ይመስለኛል በስንት ዓመቱ ከተዘጋበት እንደ አዲስ የፍልስፍና ዲፓርተመንቱን ያስከፈቱት!)

እና እነ ፔሌ ድሮ በሚማሩበት ጊዜ ፍልስፍና ዲፓርትመንት ከሚገቡ ተማሪዎች መሐል ተመርጠው፣ ተመርጠው፣ በመጨረሻ ተቋቁመው የሚያልፉትና የሚመረቁት አራት ወይ አምስት ተማሪዎች ብቻ ነበሩ ሲባል እንሰማለን! ዶ/ር ፔሌ እንግዲህ አንድ ለእናቱ ሆኖ ብቻውን የተመረቀ ነበር ማለት ነው! (ከሆነ ይገርመኛል!)

ፔሌ ተማሪ እያለ በኬኔዲ ላይብረሪ (በዋናው ስድስት ኪሎ በሚገኘው ቤተመጽሐፍት ውስጥ) የሚፈልጋቸውን መጽሐፎች ሌሎች ተማሪዎች እየተሻሙ ያስቸግሩት ስለነበር፣ እና መርካቶን የመሰለ የሰው ግርግር ባለበት ማንበብ ስለሚጠላ፣ ልክ ላይብረሪው ሊዘጋ ሲል ከምሽቱ 4:00 ሰዓት ገደማ፣ ተማሪዎች ሲወጡ፣ እሱ ግን በአንዱ የላይብረሪው ጥግ ይደበቅና ይቀር ነበረ!🤪🤓

የላይብረሪው ሠራተኞች መጥተው ሰው አለመኖሩን አረጋግጠው ሲወጡለት፣ እሱ ከተደበቀበት ይወጣና የፈለገውን መጽሐፍ መዝዞ እያነበበ ያድራል። ጠዋት ላይ ላይብረሪው ተከፍቶ ተማሪዎች ለንባብ ሲገቡ፣ እሱ ደሞ ጨርሶ ይወጣ ነበር!

ከቀድሞ ፖሊሶች በወሬ የነገረኝ አንድ ሻምበል፣ ፔሌ ተማሪ እያለ — አለኝ — አንዴ የላይብረሪው መብራት ሁሉ ጠፋፍቶ እና በሮቹ ተቆልፈው፣ ነገር ግን ሌሊት 7:00 ሰዓት ላይ በጀርባው በልደት የምግብ አዳራሽ አቅጣጫ ባለው የኬኔዲ መስኮት በኩል አንዲት ክፍል መብራት እንደበራባት አንድ ሰው ውስጥ እንዳለ ለጥበቃ ስንዘዋወር ተመለከትን!

በሌሊት ላይብረሪ ገብቶ መብራት ያበራ ማነው? ሌባ መሆን አለበት! ሪፖርት አድርገን ፖሊስ ሁሉ ተሰበሰበ። ከውጭ ሆነን ስንጮህ እሱ መልስም አይሰጠን፣ ቀና ብሎም አያየንም ነበር። መጽሐፉ ላይ እንደተቸከለ ነው።

በመጨረሻ ቁልፍ ተሰብሮ ይገባና በቁጥጥር ሥር እናውለው ብለን ወስነን፣ ወደ ላይብረሪው ዘልቀን ገባን። ገቤተን መብራት ወደበራበት መስኮት አቅጣጫ ስንሄድ ፔሌን እዚያው መጽሐፉ ላይ እንዳጎነበሰ አገኘነው።

እንዲነሳና እንዲከተለን በኃይለ ቃል ነገርነው። በተለያየ ጥያቄም አዋከብነው። እሱ ግን ከተቀመጠበት ሳይነሳና፣ ወደ እኛም ሳይዞር፣ ባለበት ሆኖ፣ እንዲህ አለን፦

"አንድ ጂኒየስ ፈላስፋ እያነበበ ነው፣
ምንም አልተፈጠረም፣ አትረብሹት!"😀🤪🤣

ይሄን ሲለን ምን ማድረግ እንዳለብን ቸገረን። መታወቂያ እንዲሰጠን፣ ማን እንደፈቀደለት፣ ብዙ ነገር ጠየቅነው። መታወቂያውን አውጥቶ (አሁንም ፊቱን ወደኛ ሳያዞር) በአየር ላይ በእጁ ይዞ አሳየን። የፍልስፍና ተማሪ ነው። ተቀብለነው ትተነው ወጣን!

ይህንንና ይህን የመሠሉ የፔሌን ታሪኮች እየሰማን በህይወት እንዳለ አንድ የምናብ የልብወለድ ዓለም ሰው አድርገን ነበር የምንመለከተው ፔሌን።

ብዙ ጊዜ ፔሌን በስድስት ኪሎ ካምፓስ NCR በሚባለው ህንፃ ካሉት የፍሬሽማን Gዎች የመማሪያ አዳራሾች፣ እና የLaw Launge ወይም ዕድር እየተባለ ከሚጠራው ዕድሜ ጠገብ በፅዶችና በትናንሽ የእንጨት ጎጆዎች የተሞላ ካፍቴሪያ መሐል ባሉት መንገዶች ላይ አታጣውም ነበረ።

ሲያገኝህ በጣም በፈገግታ ሠላምታ ለመስጠትና ለማዋራት ምንም ዓይነት ቁጥብነት የሌለበት፣ ከተማሪዎች ጋርም ተግባቢና ጓደኛ እስከመሆንም የደረሰ ነበር ፔሌ። ለምሣሌ የእኛ የሎውስኩል ልጅ ከነበረው ከታደሰ ቶርቶራ ጋር በጣም ሽርክ ጓደኞች ነበሩ።

አብረው እየተቃለዱ ካፌ ሻይ ሲጠጡ ማየት - ተማሪና አስተማሪን - በዚያን ጊዜ - ከአንዳንድ እንደ ትያትር አርትስ ካሉ ዲፓርትመንቶች በቀር የተለመደ አልነበረም!

ብዙ መምህሮች ለተማሪ ትሁቶች ቢሆኑም፣ የዩኒቨርሲቲው የመሳፍንት ዘመን አስተሳሰብ ያረበበበት የጌቶችና የሎሌዎች የመሠለ ድባብ በቀላሉ የሚሻገሩት አልነበረም!

ለምሣሌ የመምህራን ካፌና የተማሪ ካፌ የተለየ ነበረ፣ ያንን አልፈው ወደ ተማሪ ካፌዎች የሚመጡ አልነበሩም ለማለት አይደለም። ግን ተማሪ ሆነህ ከሌላ staff ጋር ካልሆንክ በቀር በመምህራን ካፌ ድርሽ አትላትም ነበር! ...

የመምህራን ቢሮ የተከበረ ነው፣ ለተለየ ጉዳይ ካልሆነ በቀር ዘው ብለህ አስተማሪ ቢሮ መግባት ከባድ ነውር ተደርጎ ይቆጠር ነበር!

እንዲህ እንዲህ ዓይነቶቹ በተማሪና በአስተማሪ መሐል ያሉ ክብርን የመጠበቅ ወይ ድንበርን የመጠባበቅ ዓይነት ባህሎች ከንጉሡ ዘመን አልፈው በእኛም ጊዜ ነበሩ በደንብ!

አንዴ የማልረሳው፣ ህንዳዊው አስተማሪያችን ሚስተር ሻርማ፣ አንድ ቀን በቁጣ ተሞልቶ የነገረን ማስጠንቀቂያ ነው፦

"መንገድ ላይ ስታገኙኝ ስሜን ጠርታችሁ
ለሠላምታ የምታስቆሙኝ ተማሪዎች፣
ነግሬያችኋለሁ፣ ሁለተኛ ጉዳይ ከሌላችሁ
በቀር ስሜን እንዳትጠሩ፣ እንዳታስቆሙኝ፣
ስንት የምሠራው ሥራ ያለብኝ ሰው ነኝ፣
ጊዜዬን እያባከናችሁ እንደሆነ አይታወቃችሁም?
ከዛሬ በኋላ ለሠላምታ ብታቆሙኝ ተከትዬ ክስ እመሠርትባችኋለሁ፣ ተግባባን?"😀🤪

መዓት ሣቅ!😀🤪 ሻርማ ፊት ለፊት በመናገርና በመናቆር ዝና ያተረፈ፣ ግን በተማሪ ዘንድ እጅግ ተወዳጅና በችሎታውም የተደነቀ፣ ለብዙ አሰርት ዓመታት በዩኒቨርሲቲው ያገለገለ ሌላኛው ዝነኛ መምህር ነበር!

እንግዲህ ዶ/ር ፔሌ ይሄንን ዓይነቱን የጌታና የሎሌ የመሠለ የመከባበርና የመፈራራት ግንኙነት ሰብሮ ነው፣ ከተማሪዎች ጋር እንደ ጓደኛ የሚጫወተውና በትህትናና በፈገግታ ለተማሪ ፊት የሚሰጠው! ያ ሰብዕናው እጅግ የሚገርመኝና ኋላም በኮሌጆች የአስተማሪነት ዕድሉን ሳገኝ አርዓያ ሆነውኛል ከምላቸው ሰብዕናዎች አንዱና አይረሴው ነው ጋሼ ፔሌ ዳሮታ!!

አንድ የማይረሳኝ፣ በወቅቱ ያበሸቀኝ፣ ኋላ ግን ዘግይቼ ትርጉሙ የገባኝ የፔሌ ፍልስፍናዊ ድምዳሜም ነበረ።

ሎጂካል ስላልሆኑ፣ ወይም በሎጂክ ፉርሽ ስለሆኑ ስሜታዊ ድምዳሜዎች እያስተማረ በአንደኛው ቀን ጴሌ ዜግነትን እንደ ጥሩ ምሣሌ አድርጎ አቀረበው! እና እንደተለመደው ተማሪዎችን randomly በየተራ መጠየቅ ጀመረ፦

"ኢትዮጵያዊ በመሆንህ የተለየ ኩራት ይሰማሃል?
ኢትዮጵያዊት ሆነሽ በመፈጠርሽ የተለየ ደስታ ይሰማሻል?"

ተማሪ በየተራ እየተነሳ ኢትዮጵያዊ መሆኑ እንደሚያኮራው መናገር ጀመረ። እንደተለመደው ፔሌ በንዴት ተንጨረጨረ! በመጨረሻም አልቻለም!

የአንደኛውን የመጨረሻውን ተማሪ ምላሽ "ኡቡቡቡቡቡ... እባባባባባባ.... ኢቢቢቢቢቢ.." በማለት ተማሪው በተናገረበት ቅላፄ ደግሞ በመናገር ሲያላግጥ ተማሪው ሁሉ ሳቀ።

ፔሌ በነገራችን ላይ የተማሪውን ፍቅርና እምነት ስላገኘ፣ የፈለገ ነገር በክፍል ውስጥ ቢያብድ፣ ወይ ቢናደድ፣ ወይ ቢሳደብ፣ ወይም የፈለገውን ቀልድና ሹፈት ቢሰነዝር... ተማሪው ሁሉ እነደ አንዳች የኮሜዲ ሾው በናፍቆት የሚጠባበቀውና የሣቅ ምንጩ ነበር..።

እንጂ ፔሌን እንዲህ ተናገረኝ፣ አደረገኝ ብሎ የሚቀየመው ሰው አልነበረም! እሱን ይሄን ሳያውቅ አይቀርም! እና በጣም ከሚገባው በላይ ኮስተር ያለ ኮሚክ መምህር ነበረ ፔሌ!

ታዲያ ኢትዮጵያዊ ሆኜ በመፈጠሬ ያኮራኛል ባሉ ተማሪዎች ላይ ምን አበሳጨው? ያበሳጨው ሎጂክ ነው። የሰው ልጆች ፍልስፍና። ከድንበር የማያልፈው የተጠየቆች የሃሳብ ዓለም።

ፔሌ በኢትዮጵያዊነትህ የምትኮራ ከሆነ ጭንቅላትህን አስመርምር አለ። የተለየ የምትኮራበት ነገር ካለ ንገረኝ፣ አንተ ምንም ያልለፋህበት፣ ሌሎች በአጋጣሚ ተገናኝተው ወልደው ያመጡህ ያልታሰብክ ሰው፣ እንዴት ብለህ ነው በሆነ ቦታ በመገኘትህ ብቻ የምትኮራው?🤣🤓🤪

ተማሪዎች ተከራከሩት። እጅ አንሰጥም አሉት። በመጨረሻ ፔሌ እሺ በምትሉት ተስማምቼያለሁ፣ ለዛሬ ተሸንፌያለሁ። እናንተ ትክክል ናችሁ! May be, logicኩን ማሻሻል ሳይኖርብን አይቀርም! በኢትዮጵያዊነታችሁ ብትኮሩ ችግር የለብኝም አለ።

አንድ መምህር የተማሪዎቹን argument ሰምቶ፣ እሺ እኔ ተሳስቼያለሁ፣ እናንተ ልክ ናችሁ ማለት በፔሌ ካልሆነ የተለመደ ነገር አይመስለኝም! ግን እንዲያም ሆኖ የማልረሳውን ይህቺን ሃሳቡን ነገረን፦

"እኔን ብትጠይቁኝ ኢትዮጵያዊ ስለሆንኩ
እኮራለሁ። ግን ኬንያዊም ብሆን ኖሮ
በኬንያዊነቴ እኮራ ነበር! ሱዳናዊም ብሆን
በሱዳንነቴ እኮራለሁ። በቃ ሁላችንም
እንደኮራን እንደተጀነንን እንኖራለና ምን
ችግር አለ!? ግን.... ግን... ፊቴ ተገትረህ
እኔ ብቻ ነኝ የምኮራው፣ ከሌሎች ኩራት
የእኔ ኩራት ይበልጣል... ካልከኝ...?! በቀጥታ
በካልቾ ጠልዤ ከዚህ ክፍል አባርርሃለሁ!!"

🤣🤣🤪 (አቤት ሣቅ...!!) በቃ የዕለቱ ወሬ ሆኖ በካምፓሱ ፔሌ ዛሬ እንዲህ አለ እየተባለ እንደጉድ ይሠራጫል! ይፈተላል! በየዶርማችን እንከራከርበታለን! እንስቃለን! Seriously, የነጀሰን ጊዜ፣ እንናደድበታለንም!

ዶክተር ጴሌ ዳሮታ በሙያው ውስጥ፣ አሊያም በፍልስፍናው ትምህርት ዘርፍ ያበረከታቸው አስተዋፅዖዎች እንደሚኖሩ አምናለሁ። ያንን የቅርብ ተማሪዎቹ ወይ ባልደረቦቹና የሙያ አጋሮቹ የነበሩ ቢናገሩት ትውልድ በሚገባ በሥራው እያስታወሰው ይኖራል ብዬ አስባለሁ።

ከሃያ ምናምን ዓመታት በፊት በአምስት ዓመታት የካምፓስ የተማሪነት ቆይታዬ በትውስታዬ ውስጥ፣ በዚያ ያማረ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የቀድሞ ቤተመንግሥት በነበረው የገነተ ልዑል ውብ የዩኒቨርሲቲ ቅፅር ግቢ ውስጥ፣ በጉልህ ደማቅ ሆነው ከማይረሱኝ ከልብ የምንወዳቸው መምህሮቻችን መሐል ግን፣ ዶ/ር ጴሌ ወይም በኛ አጠራር ፔሌ እጅግ የማይረሳ ድንቅ መምህር ነበረ!

ከቀለማቀለም፣ ከደረቅ አይዲያዎች፣ ወይም ከተሸመደዱ ምዕራባዊ መነባንቦች ይልቅ... እንደ ፔሌ ዓይነቱ መምህር ፍልስፍናን ከምንኖረው ህይወታችን ጋር በቀጥታ አገናኝተን እንድናየው ለማድረግ የራሱን የማስተማር ዘዴ ፈጥሮ በእኛ ልብና ጭንቅላት ውስጥ የሚፈልገውን ሃሳብና ጥያቄ ማኖር የቻለ ጂኒየስና የተለየ ራሱን የነበረ ሰው ነበር ብዬ አስበዋለሁ!!

በራሱ መንገድ የሚጓዝ!
በራሱ አስተሳሰብ የሚመራ!
በራሱ መንገድ እጅግ የመጠቀና ያሻቀበ!
የፍልስፍና ቴክስትቡኮች ከሚሉት ደርዝ በላይ የተሻገረና የሰፋ የራሱ ወጣ ያሉ ፍልስፍናዎች የነበሩት!
የሚገርም እና የማይረሳ ምርጥ ሰው ነበረ ፔሌ!

ደልደል ባለ ሰውነቱ፣ ቀለል ባለ አለባበሱ፣ ደማቅ ከሚያደርገው ለጥቁር ያደላ ጠይም መልኩ፣ እና ከነሚያብረቀርቀውና ብዙ ጊዜ ለተማሪዎች እያነሳ ከሚቀልድበት መላጣው፣ ከነሣቁና ፈገግታው፣ ከተማሪዎች ጋር ሲገናኝ እንደኛ እንደ ጎረምሶቹ በሰፊ ትከሻው ገፋ አድርጎ ሠላምታ የሚሰጠው ነገሩ፣ ...

ከነነፃነቱ፣ ከመምህራን የበለጠ በተማሪዎች መከበብና ከተማሪዎች ጋር መቀራረብ ደስ ከነሚላት ውብና ትሁት ነፍሱ ጋር... ሁሌም ፔሌን ሳስታውሰው እኖራለሁ። ስናስታውሰው እንኖራለን።

ዶ/ር ጴሌ ዳሮታ ፍልስፍና በነፃነት የማሰብ ሳይንስ መሆኑን በተግባር ኖሮ፣ በነፃነት ተመላልሶ፣ በነፃነት ማሰብን በልባችን ተክሎ ያለፈ፣ የነፃና ዘመናዊ ሰው ተምሣሌት ነበር! በ1993 ዓ/ም ላይ የዩኒቨርሲቲ አመፅ ሲነሳ ከተማሪ ጋር ወግኖ የቆመ ጀግናም ነበር!

ደግሞ ከባለጊዜዎች ጋር የማይተጣጠፍ ታላቅ ራሱን የቻለ ነጻ ፈላስፋ ነበረ! የኛ ዲዮጋናችን ነበር ዶ/ር ጴሌ!!

ዶ/ር ጴሌ ዳሮታ ምርጥ መምህርና አርዓያ ሰብዕ ነበርክ!

ፈጣሪ ነፍስህን በአፀደ ገነቱ ይቀበላት!

(ይህንን ስል ቢሰማኝ ጸሎቴን ይቀበለው ይሆን? ወይስ ይሞግተው? — አላውቅም! ፈጣሪ ንፁህ ነፍሱን ደጋግሞ ይቀበላት!)

ለቤተሰቦቹ፣ ወዳጅ ዘመዶቹ፣ አድናቂዎቹ መጽናናቱን ይስጥልን!

አሉን የምንላቸው ምሁራን እንደ ዘበት ተራ በተራ በሞት የመለየታተው ነገር የሆነ ውስጥን የሚያደማ ሀዘን አለው! አንድ ጄነሬሽን እያለፈ፣ ሌላ ትውልድ በእግራቸው እየተተካ መሆኑንም የሚናገር አስታዋሽ ነው!

ይህ ትውልድ እንደቀደሙት ትውልዶች ራሱን በዕውቀት ያደረጀና በአስተሳሰብ ያመጠቀ ሆኖ ይገኝ ይሆን? ወይስ እነዚህ ዋርካዎች የማይተኩ፣ የአንድ ግዙፍ ዘመን የመጨረሻዎቹ ቆንጆዎች ይሆኑ? አላውቅም! ፈጣሪ ለትውልዳችን አብርሆትን እንዲሰጠው ከልቤ እመኛለሁ!

የመምህራችንን ነፍስ ይማርልን!

ሸጋ ቀን!

🙏🏿❤️

Via Assaf Hailu

10 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.