Logo
Getu Temesgen
የማርበርግ ቫይረስ በሽታ (MVD) መድሐኒት ለምን አልተገኘለትም?
#ethiopia | የሰሞነኛው ማርበርግ ቫይረስም ሆነ ሌሎች የዚህ ዝርያ ያላቸው በሽታዎች ቶሎ ሊያድን የሚችል መድኃኒት አለመኖሩ ትልቁና ፈታኙ ጉዳይ ነው፡፡ ለምሳሌ ኢቮላ ቫይረስን ማስታወስ እንችላለን፡፡ እነዚህ ቫይረሶች ሲከሰቱ አፋጣኝ የሆነ ክትትል ማድረግ እና ስርጭቱ በቶሎ እንዳይዛመት ማድረግ የመጀመሪያው ነጥብ ነው፡፡

መድሐኒት በቶሎ የማይገኝላቸው ስለምን ይሆን? ይህንን ማህበረሰባችን እንዲረዳው ማድረግ ተገቢ የሆነበት ዋናው ምክንያት ህብረተሰቡ የቁጥጥርና የክትትሉ ግንባር ቀደም ተሳታፊ እንዲሆን ነው፡፡ አዎ መድሐኒታቸው በቶሎ አይገኝም፡፡ ዋናው ምክንያት ደግሞ ቫይረሱ በሰውነት ውስጥ በሚያመጣው ፈጣንና ከባድ ቀውስ እንዲሁም በፋርማሲዩቲካል ሳይንስ (Pharmaceutical Science) ውስጥ ባሉ ውስብስብ ችግሮች ነው።

1. ቶሎ የሚያድን መድኃኒት ያለመኖሩ ምክንያቶች
ሀ. የቫይረሱ ተፈጥሯዊ ባህሪ

🔬በፍጥነት የመራባት ችሎታው: ማርበርግ ቫይረስም ሆነ የእርሱ መሰል ቫይረስ አንዴ ወደ ሰውነት ከገባ በኋላ በከፍተኛ ፍጥነት ይራባል፡፡ (replicate) በተጨማሪም ወሳኝ የሆኑ ሴሎችን (በተለይ የደም ስሮችን የሚገነቡ ሴሎች እና የጉበት ሴሎች) በከፍተኛ ሁኔታ ይጎዳል። ይህ ጉዳት በፍጥነት ወደ ብዙ የአካል ክፍሎች በመዛባት (multi-organ failure) እና ይህ ደግሞ ድንገተኛ ወደ ሆነ የደም መፍሰስ ያመራል።

🔬የሰዎችን በሽታ የመከላከል አቅም በቶሎ ማዳከም መቻሉ: ቫይረሱ የሰውነትን በሽታ የመከላከል ስርዓት በፍጥነት ያዳክማል። ይህ ደግሞ ሰውነት ራሱ ቫይረሱን ተዋግቶ እንዲያሸንፍ እድል አይሰጥም።

ለ. ለሳይንስ እና ለምርምር ያለው ተግዳሮት

🔬 በሽታው አልፎ አልፎ ብቻ መከሰቱ: የማርበርግ ወረርሽኞች የሚከሰቱት አልፎ አልፎ (sporadically) እና በተወሰኑ አካባቢዎች ብቻ ነው። ይህ በትልቅ ደረጃ (በሰፊው ምርምር እንዳይደረግ) (Clinical Trials) አስፈላጊ የሆኑ ታካሚዎችን ቁጥር ለማግኘት አስቸጋሪ ያደርገዋል።

🔬 የምርምር ቦታ ደህንነት: ቫይረሱ እጅግ በጣም አደገኛ በመሆኑ (Bio-Safety Level 4) በመሆኑ፣ በቤተ ሙከራ ውስጥ ምርምር ለማድረግ እና ማድኃኒት ለማልማት በከፍተኛ ሁኔታ የደህንነት ጥንቃቄ የሚጠይቅ በመሆኑ እና ሂደቱም ውድ እና የሰው ሃይል የሚጠይቅ በመሆኑ ነው።

🔬 የፍጥነት አስፈላጊነት: ወረርሽኝ ሲከሰት፣ መድኃኒት ከማልማት እና ከማረጋገጥ ይልቅ በፍጥነት የሕመም ምልክቶችን ማስታገስ እና ስርጭትን መግታት ቅድሚያ መስጠት አስፈላጊ በመሆኑ ነው።

2. የህክምናው አሰጣጥ(Treatment Protocol)
ምንም እንኳን ፈዋሽ መድኃኒት ባይኖርም፣ በአሁኑ ወቅት የሚሰጠው ሕክምና ደጋፊ የሆነ እንክብካቤ (Supportive Care) በመባል ይታወቃል፣ ይህም በፍጥነት ከተሰራ የታካሚውን የመትረፍ ዕድል በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል። እንደገና ለማስታወስ ያህል የሚከተሉትን እናደርጋለን።

ፈሳሽ መተካትና ኤሌክትሮላይት ቁጥጥር ማድረግ: በሰውነት ውስጥ ድርቀት እንዳይኖር እና የጨው እጥረትን ለመከላከል ፈሳሾችን በደም ስር (IV fluids) መልክ በቋሚነት መስጠት።
#የደም ግፊትን መከታተል: የድንጋጤ ሁኔታ (shock) እንዳይከሰት ለመከላከል የደም ግፊትን የሚያረጋጉ መድኃኒቶችን በባለሙያ ክትትል መስጠት።
#የደም መፍሰስ እንዳይኖር ማድረግ: ከባድ የደም መፍሰስን ለማቆም ሲባል ለደም መርጋት የሚረዱ (clotting factors) የያዘ ደም ወይም የደም ክፍሎችን (ፕላዝማ) መስጠት።
#የህመም ማስታገሻ: ትኩሳትን እና ከባድ የሰውነት ህመምን ለመቀነስ እንደ ፓራሲታሞል ያሉ የህመም ማስታገሻዎችን መስጠት (ደም መሳሳትን የሚያባብሱ እንደ አስፕሪን ያሉትን ደግሞ ህሙማን እንዳይወስዱ መከላከል።)

ባምላኩ አበባው
ፕሮፌሽናል ነርስ እና የማህበረሰብ ጤና ባለሞያ
ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ህክምና ማዕከል

7 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.