Logo
Getu Temesgen
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባህል ማዕከል ልጆች አስደንቀውኛል

ከዕዝራ እጅጉ( ተወዳጅ ሚድያ)
#ethiopia | #ተወዳጅታሪክ ትናንት ህዳር 3 2018 ዓ.ም የብሔራዊ ቴአትርን 70ኛ ዓመት ክብረ በዓል ከታደምኩ በኃላ ወዳጄ (ተስፍሽ )ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ እሸቱ በጋበዘኝ መሠረት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባህል ማዕከል የኪነት መሰናዶ ላይ ታደምኩ። መቼም ስለ ባህል ማዕከሉ ካነሳሁ አይቀር አራት አንኳር ጉዳዮችን ላንሳ።
#ጉዳይአንድ ፦በዕለቱ በሮቡ መሰናዶ ተማሪዎቹ ያቀረቡት ኪናዊ መሠናዶ ተመችቶኛል።ለሚቀርቡት ግጥሞችም ሆነ ሙዚቃ ታዳሚው የሚሰጠው ምላሽ በንቃት እንደሚከታተል ያሳብቃል። ጭብጨባቸው፣ ሞራል ይገነባል። አዳራሹም ሙሉ መሆኑ ደስ የሚያሰኝ ነው። መድረክ መሪው አስራትም በሥርዐት እና ለተማሪ በሚመጥን መልኩ መድረኩን በወጉ ይዞት እንደነበር ማስተዋል ችያለሁ። እንደልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስ ሆና የሠራችው የ11 ዓመት ታዳጊ በራስ መተማመኗ ደናቂ ነበር። በርቺ ብያታለሁ። ግጥም ቀርቦ ራሱ ይኼኛውን አንብብ እየተባለ የተመልካቹን ስሜት ለመጠበቅ የተደረገው ጥረት አስደስቶኛል።
#ጉዳይሁለት ፦የባህል ማዕከሉ መታደስና ደረጃውን መጠበቅ ደስ የሚያሰኝ ነው። መቼም ለዚህ ትልቁን ድርሻ የሚወጣው የማዕከሉ ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ እሸቱ ነው። ተስፍሽ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የጥበብ እንቅስቃሴ እንዲያድግ ሲለፋ የኖረ ወጣት ምሁር ነው። ከጎኑ መቆም እንዳለብን ይሰማኛል። ታሪኩን መዝገበ አእምሮ ቅፅ ሁለት ላይ እንደመሰነዴ ተስፍሽ ለባህል ማዕከሉ እዚህ መድረስ ያደረገው ጉልህ ሚና መነገር አለበት ብዬ አምናለሁ። አዳራሹን ሳየው ያስተዋልኩትም ይህንኑ ነው። ከተስፍሽ ጋር የደከሙ የዩኒቨርስቲ አመራሮችም መመስገን አለባቸው።
#ጉዳይሦስት፦ የእኔና የባህል ማዕከሉ ትዝታ በዓይኔ እየመጣ ነበር ትናንት ። በ1992 የሦስተኛ ዓመት ተማሪ ሳለሁ። ሥርቻ ባለችው ክፍል ወግ ስናቀርብ የነበረበት ጊዜ ትውስ አለኝ። በጊዜው ተክለሚካኤል አበበ(law school) በዕውቀቱ ሥዩም(ሳይኮሎጂ) ፣ፍቅር ይልቃል ይመጡ እንደነበር አልዘነጋውም። ያኔ ያልተወለዱ ልጆች ከ 26 ዓመት በኃላ አድገው ፣ዩኒቨርሲቲ ገብተው፣አዳራሹን ሞልተውት ሳይ ድንቅ አለኝ። ምናልባት የዛን ቀን አግብቼ ቢሆን ልወልዳቸው የምችላቸው(የልጅነት ልጆቼ) ትኩስ ኃይላት ጋር አብሬ መሆኔን ሳስብ መንፈሴ ተደሰተ። በመጪው ትውልድ ወይም በታናናሾቼ ተስፋ ስለማልቆርጥ አሁንም መልካሙን ሁሉ እመኝላቸዋለሁ። ተስፋ ያላቸው ናቸውና።ወጣት የነብር ጣት ይሏል።
#ጉዳይአራት፦ባህል ማዕከሉ ለእኔ ምን አደረገልኝ ሳይሆን እኔ ለባህል ማዕከሉ ምን ላድርግለት የሚለው የእኔም የድርጅቴም ቀዳሚ ግብ ነው። ወዳጄ ተስፍሽ ባቀረበው ሀሣብ "መዝገበ አእምሮ "በሚል ርዕስ ለህትመት ካበቃሁት የአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ መፅሐፍ ውስጥ ሁለት ቅጂ ለማዕከሉ ለማበርከት ወሰንኩ። በዕለቱም አጭር መልዕክት አቅርቤ መፅሀፉን አስረክቤአለሁ። የባህል ማዕከሉን ቤተ መፅሀፍት ለማደራጀትም ከሚደረገው እንቅስቃሴ ጋርም አብሬ መቆሜን ማረጋገጥ እወዳለሁ።

ተወዳጅ ሚድያ ከበጎ ነገሮች ጋር ሲቆም የኖረ እንደመሆኑ ባህል ማዕከሉን ለማገዝ የሚችለውን ያደርጋል። በዕለቱ ለ3 ደቂቃ ወጥቼ ለተማሪዎቹ እንዳልኳቸው ማን ያውቃል ነገ ጠንክረው ከሠሩ ኢንሳይክሎፒዲያ ላይ ታሪካቸው ሊሰፍር ይችላል ። ደግሞም ይችላሉ። የባህል ማዕከልም ቀዳሚ ግብ ነገ አሳቢ፣አሰላሳይ፣ ታሪክ ሠሪ ምሁርን ማፍራት ስለሆነ ከወዲሁ ባህል ማዕከሎች በርቱ ማለት እወዳለሁ።

7 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.