Logo
SeledaPost
የታሸጉ ምግቦች አያዘውትሩ‼️
" በአሁኑ ሰአት ከወጣቶች በዘለለ እድሜያቸው 12 እና 13 የሆኑ ህፃናት በስኳር በሽታ ኩላሊታቸው እንዳይሰራ እየሆነ ነው። ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱ የስኳር እና የጨው ይዘት ያላቸው የታሸጉ ምግቦች ናቸው " - የኢትዮጵያ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ማህበር

ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች የሚያጋልጡ የታሸጉ ምግቦችን ለመቆጣጠር የሚያስችል አዋጅ ተዘጋጅቷል።

አዋጁ መዘጋጀቱን ተከትሎ ፦
- የተዋልዶ ጤና አገልግሎት ሰጭ ማህበራት ህብረት (CORHA)፣
- የኢትዮጵያ የልብ ማህበር፣
- የኢትዮጵያ የስኳር በሽታ ማህበር እና የኢትዮጵያ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ማህበር በጋራ በመሆን ከቀናት በፊት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተው ነበር።

የኢትዮጵያ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ማህበር ሰብሳቢ አቶ ቢኒያም አበራ " በአሁኑ ሰአት ከወጣቶች በዘለለ እድሜያቸው 12 እና 13 የሆኑ ህፃናት በስኳር በሽታ ኩላሊታቸው እንዳይሰራ እየሆነ ነው " ብለዋል።

" ለኩላሊት በሽታዎች ዋነኛ ምክንያቱ የስኳር እና የጨው ይዘት ያላቸው የታሸጉ ምግቦች ናቸው " ሲሉም ገልፀዋል።

አቶ ቢኒያም አበራ በዝርዝር ምን አሉ ?

" በማህበራችን ውስጥ አብዛኛው ኩላሊታቸው የተጎዱ ሰዎች ለኩላሊታቸው መጎዳት ዋነኛ ምክንያት የሆነው ደም ግፊት እና የስኳር በሽታዎች ናቸው። እነዚህ በሽታዎች ደግሞ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ከአመጋገብ ስርአት ጋር የተገናኙ ናቸው። ምክንያቱም የታሸጉ ምግቦች በአብዛኛው የስኳር እና የጨው ይዘት አላቸው።

በተለይ ደግሞ በፋብሪካ የሚቀነባበሩ ምግቦች በውስጣቸው በምግብ ማቀነባበር ስርአት ውስጥ የተጠራቀመ የስብ ክምችት አለ። ይህ የሚጨመር ስኳር ሰዎች በሚመገቡበት ጊዜ በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ሰውነት ውስጥ ከፍተኛ  የስኳር መጠን እንዲገባ ያደርጋል። ይህ በሰውነታችን ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን ያዛባዋል፤ በዚህም የስኳር በሽታ እንዲከሰት ያደርጋል። በምግብ ውስጥ የሚጨመር ንጥረ ነገር ደግሞ የደም ግፊትን ያመጣል። በመሆኑም ኩላሊት ስራውን በአግባቡ እንዳይሰራ ያዳክሙታል። በመጨረሻም ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ኩላሊት ስራውን እንዳይሰራ ያደርጋል።

እነዚህ ነገሮች በተናጠልም ሆነ በድምር በርካታ ቁጥር ያላቸውን ዜጎች እያጠቁ ያሉ ንጥረ ነገሮች ናቸው። ስለዚህ እነዚህን ንጥረ ነገሮች ወደ ዜጎች በሚመጡበት ጊዜ ቁጥጥር ሊደረግባቸው ይገባል።

በታሸጉ ምግቦች ሽፋን ላይ በውስጣቸው የያዙት ንጥረ ነገር በአይነት እና በመጠን ሊገለጽ እንዲሁም ሰዎች እነዚህን ሲመገቡ ሊደርስባቸው የሚችሉ ጉዳቶች በመሸፈኛቸው ላይ በጉልህ መቀመጥ አለባቸው።

በታሸጉ ምግቦች ላይ በቂ ቁጥጥርና ጥበቃ ሊደረግ ይገባል።

እነዚህ ምግቦች በማህበረሰባችን ላይ እያደረሱት ያለው ጉዳት እና ቀውስ ለመቀነስ ማህበራችን ይህ አዋጅ ቶሎ ተፈጻሚ እንዲሆን ይሰራል " ብለዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ ምግብ ህክምና ባለሙያ እና የኢትዮጵያ ስነ ምግብ ህክምና ባለሙያዎች ማህበር ተወካይ የሆኑት ዶ/ር ዘላለም ከበደ " ኢትዮጵያ በፋብሪካ በተቀነባበሩ እና ጤናማ ባልሆኑ ምግቦች ምክንያት ለሚደርሱ የጤና ጉዳቶች በየዓመቱ ከ31 ቢሊየን ብር በላይ ታወጣለች " ሲሉ ተናግረዋል።

አያይዘውም " በየስአቱ 25 ሰው ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ማለትም በስኳር፣ በኩላሊት፣ በጉበት እና በልብ እንዲሁም በደም ቧንቧ በሽታዎች ይሞታሉ፣ በአሁኑ ስአት የህመሙ ጫና ከ52 በመቶ በላይ ሆኗል " ነው ያሉት።

" የምግብ ጥራትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ምክንያቱም በርካታ ሰዎች የታሸጉ ምግቦች ጥሩ እየመሰሏቸው ሲገዙ ይታያል። ይህ በጥናት መረጋገጥ አለበት። ማህበረሰቡ ባለው የግንዛቤ ክፍተት ምክንያት እየተጠቀመ እየተጎዳ ነው " ብለዋል።

" ማህበረሰቡ በአዋጁ መሰረት ክልከላ የሚደረግባቸው የስብ፣ የስኳር እና የጨው መጠናቸውን ያልጻፉ የታሸጉ ምግቦችን ሲያዩ ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ አለባቸው። አዋጁ ቶሎ ወደ ተግባር ገብቶ ክፍተቶቹ እየታዩ መስተካከያ ሊደረግበት ይገባል " ሲሉ ገልጸዋል።ቲክቫህ

seledadotio
seledadotio
7 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.