Logo
YenetaTube
እኛ ወደ እርሱ መውጣት ሲያቅተን፣ መድኃኔ ዓለም ወደኛ መጣ🙏

ካሕናት አባቶቻችን የስቅለተ ዕለተ የዘጠኝ ሰዓት ስግደት ሲሰገድ “ኦ ዘጥዕመ ሞተ በስጋ” “በስጋው ሞትን የቀመሰ ኢየሱስ ክርስቶስ” እያሉ ልብን በሚያሳዝን ዜማ ያዜማሉ፡፡

የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ቄርሎስም “ለቤተ ክርስቲያን ስትል በአደባባይ በጥፊ የተመታህ አቤቱ ይህን ማድረግህ እርስዋን በከበረ ደምህ ትቀድሳት ዘንድ ነው፡፡ ለእርስዋ ሲል ታሥሮ መጎተት የቻለ የበደለውም በደል ሳይኖር፣ ርኩስ ምራቅን ሲተፋበት የታገሠ መድኃኔ ዓለም በእንጨት መስቀል ላይ ተሰቀለ” በማለት ገለጸው፡፡ በመለኮቱ ሕያው ሲሆን በስጋው ግን ሞትን ቀመሰ፡፡ የአዳምን ሞት በሞቱ ሊሽር መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ነፍሱን በገዛ ፈቃዱ አሳልፎ ሰጠ፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር ሰው ሆኖ እንደሚያድነን በመጀመሪያ ለአዳም ቃል ገባለት፡፡ ከዚያም በነቢያት ትንቢት አስነገረ፡፡ በስጋ በተገለጠ ጊዜም የሰቀሉትና የገደሉት አይሁድ ሳይቀሩ እንዲናገሩ አፋቸውን አስከፈታቸው፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች ሲጽፍ “ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን… አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን” ይላል፡፡ አልአዛርን ለአራት ቀናት በመቃብር ከቆየ በኋላ ከሙታን ሲያስነሳው ከአይሁድ ወገን ብዙዎች አመኑ፡፡ አንዳንዶች ግን ወደ ፈሪሳውያን ሄደው ኢየሱስ ያደረገውን ነገሯቸው፡፡ በዮሐንስ 11 እንደተጻፈው ከተአምራቱና ከትምህርቱ የተነሳ ሕዝቡ ሁሉ ትቷቸው እንዳይሔድ የፈሩት አይሁድ ሲማከሩ በዚያች ዓመት ሊቀ ካህናት የነበረ ቀያፋ የሚሉት ከእነርሱ አንዱ፡- “እናንተ ምንም አታውቁም፤ ሕዝቡም ሁሉ ከሚጠፋ አንድ ሰው ስለ ሕዝቡ ይሞት ዘንድ እንዲሻለን አታስቡም” አላቸው።

ይህንም የተናገረ ከራሱ አይደለም፤ ኢየሱስ ስለ ሕዝቡ ሊሞት እንዳለው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ትንቢት አናገረው፡፡ “ስለ ሕዝቡም ሁሉ አይደለም፣ ነገር ግን የተበተኑትን የእግዚአብሔርን ልጆች በአንድነት እንዲሰበስባቸው ነው እንጂ።” ተብሎ ተጽፏልና፡፡ የቀድሞው የግብጽ ኦርቶዶክሳውያን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሺኖዳ “እኛ ወደ እርሱ መውጣት ሲያቅተን መድኃኔ ዓለም ወደኛ ወረደ” በማለት ይገልጹታል፡፡ የማዳኑ ስራ ለሰው ልጅ ቤዛነት የተደረገ፣ ፍጹም ፍቅሩ የታየበት ከሰው ሕሊና በላይ የሆነ አባትነቱን ያሳየበት ነው፡፡ አምላክነትን ሲሻ የወደቀው የሰው ልጅ፣ የወደደውን አምላክነት ያገኝ ዘንድ የሰውን ባሕርይ ተዋህዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ፡፡ በድንቅ ተዋህዶ አምላክ ሰው፣ ሰውም አምላክ ሆኗልና ከኛ በነሳው ስጋም ወደ ሰማይ አረገ፡፡

ስለፍጹም የሰው ልጆች ፍቅር መድኃኔ ዓለም ተላልፎ ተሰጠ፡፡ ለዚህም ነው በፊልጵ 2÷8 “በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፣ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ” ተብሎ የተጻፈው፡፡ በማዳኑ ስራ ውስጥ የቅድስት ድንግል ማርያም ድርሻ ታላቅ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “ሔዋንን ዲያብሎስ አሳታት የሞት ምክንያት የሚሆን ቃየልን ወለደች፡፡ ድንግል ማርያም ግን መልአክ በአበሠራት ጊዜ ሁሉን ወደ ዘለዓለም ሕይወት የሚመራ አካላዊ ቃልን በሥጋ ወለደች፡፡” ይለናል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም በገላ 4÷4 “የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ልጁን ላከ፡፡” ሲል ጽፏል፡፡ ይህን መከራውንና ማዳኑን ዕለት ዕለት የሚያስቡ ገዳማውያን ሌሊትና ቀን በስግደትና በጸሎት ይተጋሉ፡፡ ገዳማቱን እንደግፍ፣ በዓታቸውን እናጸና፡፡

ድጋፍ ለማድረግ:- ሙትአንሳ ማር ቅዱሰ ሚካኤል አንድነት ገዳም

ኢትዮጲያ ንግድ ባንክ
1000442598391

ወይም

አቢሲኒያ ባንክ
141029444

የገዳሙ ስልክ ቁጥር:-0918077957 ወይም 0938644444

8 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.