Logo
SeledaPost
ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለሚገቡ ተማሪዎች የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር እየተሰጠ መሆኑ ተገለጸ

በ2018 የትምህርት ዘመን ወደ መንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለሚገቡ ተማሪዎች፤ የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር (TIN) በሁሉም ቅርንጫፎች እየሰጠ መሆኑን የገቢዎች ሚኒስቴር ለአሐዱ አስታውቋል፡፡

በሚኒስቴሩ የታክስ ከፋዮች ምዝገባ እና አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ደረጄ ፋና፤ የከፍተኛ ትምህርት ወጪ መጋራትን በተመለከተ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ሲጨርሱ ክፍያ የመክፈል በሕግ የተቀመጠ ኃላፊነት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ይህንን የወጪ መጋራት ክፍያን ለመሰብሰብ እንዲያመች በአዋጁ መሠረት ለገቢዎች ሚኒስቴር በተሰጠው ኃላፊነት፤ በግብር ከፋይ መለያ ቁጥር ተግባራዊ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

አሰራሩ አዲስ አበባን ጨምሮ በክልል ከተሞች ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን አንስተው፤ የግብር ከፋይ መለያ ቁጥሩን የፌዴራል ዋና ኦዲተር ተቋማት ወይም ቀጣሪዎችና ባለድርሻ አካላት የወጪ መጋራትን ከመሰብሰብ አንፃር የተሰራው ሥራ ክፍተት ያለበት ሆኖ በመገኘቱ ያለውን አሰራር ለማሻሻል ያለመ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ተማሪዎች የወጪ መጋራት ክፍያቸውን በግብር ከፋይ መለያ ቁጥር በቀላሉ መፈፈም እንዲችሉ ለማድረግም ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም መሠረት የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አዲስ እና ነባር ተማሪዎች በሙሉ የፋይዳ ቁጥር በመያዝ፤ በሁሉም የገቢዎች ቢሮ ቅርንጫፎች በመገኘት የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር በመውሰድ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ዳይሬክተሩ አክለውም በቀጣይ ከሌሎች ተቋማት ጋር በሚኖር ቅንጅታዊ አሰራር ደግሞ፤ ተማሪዎች ባሉባቸው ዩኒቨርስቲዎች የግብር ከፋይ መለያ ቁጥሩን እንዲያገኙ የሚደረግበትን አሰራር ለማመቻቸት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

seledadotio
seledadotio
1 year ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.