9 months ago
#ethiopia | አፍላ ወጣትነቴን የዋጀልኝ፤ ሙዚቃ እንዲህ እንደዛሬ ስልካችን ላይ መርጠን፤ መራርጠን በማንሰማበት ጊዜ፤ የኮፒ መብት መሆኑን ሳናውቅ፤ ያኔ እንዲህ ሳይገባን በካሴት አስለቅመን ከእነ አህመድ እና ዘላለም ሙዚቃ ቤት በኮሌክሽን መልክ ከምናስቀዳቸው ተመራጭ ዘፋኞቻችን መካከል በሁሉም ሰው ዘንድ ተፈላጊው የ90ዎቹ ውዱ ዜመኛ መስፍን በቀለ፤ ራሕሮታዊ በሆነ ልሳነ-ዜማው፤
በክረምት ወር ሀምሌ ነሀሴ
ከኔ ሌላ አለ ትራሴ
እንደሌለኝ የሚያሞቅ ሰው
የሚነግርሽ ኧረ ማነው
እሱስ ይሁን ይነገርሽ
ለኔ ካዘነ ልብሽ
መጥተሽ ላትገቢ ከእቅፌ
ለምን ይጥፋ እንቅልፌ
ነይ በክረምት ነይ በብርዱ
ሰው አይችልም ሆዱ .....
እያለ የአፍላ ወጣትነት የፍቅር ጀምሬ ልባችን ቅልጥ አድርጎ በአንድ ከተማ ያሉ ፍቅረኛሞችን ሳይቀር አድማስ ጥግ የተራራቁ ይመስል፤ በጥበባዊ የምናብ ኃይሉ እያለቀሰ ያሰናኘ። ሲያሻው ደግሞ ልክ አሁን እንደለቀቀው ስርዓተ-ባህለ-ወጉን የጠበቀ፤ ባህል ከእነቱባ-ክቱ፤ "ደም-መላሽ... ያይዋ" እያለ ከእግር ጥፍራችን እሰከ ራስ ፀጉራችን አንዝሮ፤ አናዝሮ፤ ነፍስያን አጥፍቶ ትክሻችን እስኪላጋ ድረስ ያስነገጠን፤ ያስደለቀን። መስፍን በቀለ የነካኸው ይመርልህ ተብሎ በጠዋቱ ተመርቋልና ይሄው በውቧ እና ታሪካዊቷ ጎንደር እንደ አዲስ ተገልጧል።
ታላቁ ፈላስፋ አርስቶትል "ጥበብ የጎደለውን ዓለም ምልዓት የምትሆን ናት" ይላል። ወይም ጥበብ ተፈጥሮ ጀምራ ያላጠናቀቀችውን ዳር ለማድረስ የምትጥር ናት እንደማለት ነው። (Art partly completes what nature is itself unable to bring to a finish, and partly imitates her.) ተፈጥሮ በራሷ ውብ ብትሆንም፣ የሰው ልጅ ነፍሳዊ ሐሴቱን ሆነ ትካዜውን የስሜት ዳርቻዊ ክፍተቱን ብሎም የሀገርን የናፍቆት ስሜቱን ሙሉ በሙሉ መሙላት አትችልም። ይህንን ክፍተት የሚሞላው ደግሞ እንደ መስፍን ያሉ የጥበብ ውጤቶች ናቸው። በዚህም የተነሳ ጥበብ ለነፍስያ ምግብ ናት ይባላል።
መሰፍን በቀለ ከመንፈሳዊ ምግብነት ባለፈ ለሀገራችን ኢትዮጵያ ያለውን ጥልቅ ፍቅር በዜማና በግጥሙ ደጋግሞ እየሰጠን ይገኛል። አሁን ይዞት የመጣው አዲስ ስራ፣ የጥበብ በሳልነቱን የሚያመለክት ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያዊነት የኩራት ምንጭ የሆነችውን ጎንደር ሞሽሮ፤ እርሱም በታሪክ ፊት ተሞሸረባት። ለሐገሩ ያለውን ክብርና ኩራት በጉልህ የሚያሳይ ድንቅ የጥበብ ስራ ውጤት ሆኖ ተመልክቸዋለሁ።
#ድምፃዊ_መስፍን_በቀለ
#የዜማህ_ውበት፦ በድምፅህ ውስጥ የሚስረቀረቀው ቃናዊ ልክህ ልብን የሚያርስ፣ ትዝታን የሚቀሰቅስና ተስፋን የሚጭር ነው። ባትሆን እንኳ "እኔም ጎንደሬ ነኝ" የሚያሰኝ ነው።
#የሐገር_ፍቅርህ፦ ሔሌም በየስራዎችህ ውስጥ የሚንፀባረቀው የሐገር ፍቅር ስሜት፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የራሱን ማንነትና እውነተኛ ኩራት እንዲመለከት የማነሳሳት ኃይል አለው።
#የፈጠራ_ብቃትህ፦ አሁን ያስደመጥከን አዲስ ሙዚቃ በቅንብርም ሆነ በይዘት ጥራት ያለው፤ በተለይ ሲኒማቶግራፊው እንዴት ድንቅ ነው። በሙዚቃ ቪዲዮ ሥራ ውስጥ አዲስ ከፍታን ያሳየ ነው ብዬ አምናለሁ።
ጥበብ የሕዝበ-ሐገር ድምፀት ናት። አንተ ደግሞ የጎንደር ድምፀት መሪ ሆነህ ብቅ ብለሃል።
ይህ አዲስ ስራህ በሰዎች ዘንድ የሚፈጥረው ደስታ እና መነቃቃት በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ለዚህ ደግሞ ተከተለውህ እየመጡ ያሉ ሥራዎች እማኞችህ ናቸው። ድካምህ ፍሬ አፍርቶ፣ ጥበብህ ለብዙዎች መፅናኛና ኩራት ከመሆን አልፎ ባለሙያዎች ላይ በጎ ተፅዕኖ ማሳረፍ በመቻልህ ኩራት ሊሰማህ ይገባል።
የበለጠ እንድትበረታ፣ እንዲህ በመሰለ እና አዳዲስ መንገዶች ደጋግመህ እንድትመላለስ፣ ሑሌም የጥበብ አድማስህን እንድታሰፋና በምትወዳት ሐገርህ ላይ ሁሌም ምልክትህን እያሳረፍክ እንድትቀጥል ታላቅ ምኞቴ ነው።
#ቻላቸው_ፈረጅ (#ረፕ)
#mesfinbekele #gondar #ethiopianmusic #legend #art #culture #chalachewferej
Comments