ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ የበደሉትንም ያልበደሉትንም ሞት ገዛቸው” እንዳለ አዳምና ሔዋን ብቻ ያይደሉ ከእነርሱ የተወለዱ ልጆችና የልጅ ልጆቻቸው ሁሉ በደለኞች ሆኑ፡፡
የመጀመሪያውና ታላቁ በደል ጥንተ አብሶ ሲሆን ቅዱስ ቄርሎስ “ጥንተ ኃጢአት” ቅዱስ ሳዊሮስና ቅዱስ ኤፍሬም “ዘቀዳሚ መርገም” ብለውታል። ይህም የውርስ ኃጢአት ከአዳም ጀምሮ ከወላጅ ወደ ልጅ እየተላለፈ ሰውን ሁሉ የሚገዛ ሆነ። ባሕርየ ሰብእ ጐሰቈለ፣ ንጽሐ ጠባይዕ አደፈ፣ ኃጢአት ብዙዎችን አጠመደች፡፡ ስለዚህም ተላልፈው ለሞትና ለሲኦል ተሰጡ። ከዚህ ንጽህት ሆና የተገኘች ቅድስት ድንግል ማርያም ብቻ ናት፡፡
በኃጢትም ምክንያት በባሕርየ ሰብእ ጸንቶ የነበረውን መርገም ሊያጠፋ ከሦስቱ አካላት አንዱ ወልድ ሰው ሆኖ በሚጸነስበት ልክና ሥርዓት ከንጽሕት ድንግል ማርያም ተወለደ።
ፍጹም ጌታ ፍጽምት በሆነች በእመቤታችን ማኅፀን አደረ፣ ቡሩክ አምላክ “ከሴቶች ይልቅ አንቺ ቡርክት ነሽ” ተብላ በመልአኩና በኤልሳቤጥ አንደበት ከተመሰገነች ከድንግል ተወለደ፤ ቡርክት ማኅፀን የቡሩክ አምላክ ማደሪያ ሆነች፡፡ ቅድስት ማኅፀን ቅዱስ ጌታን በሥጋ አስገኘች፤ ከመርገም በፊት ከነበረች ቡርክት ምድር አዳም ያለእናት ያለአባት ተፈጠረ፤ ዳግማይ አዳም ክርስቶስም ኃጢአተ አዳም ከሌለባት ቡርክት ማርያም ተወለደ፤ ከድንግል የተወለደ ጌታ ነውር ነቀፋ የሌለበት ንጹህ እንደሆነ፣ የወለደችው ድንግልም ነውር ነቀፋ የሌለባት ንጽህት ናት፤ እርሱ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ቅዱስ እንደሆነ እርሷም በጊዜ ሁሉ ቅድስት ናት፡፡ ለመወለዱ ዘርዕ ምክንያት አልሆነውም፤ በንጽሕና በቅድስና ጸንታ ከኖረች ከድንግል ያለአባት ተፀነሰ፤ ሕማም፣ ድካም ሳያገኛት በሴቶች የሚደርሰውም ሳይደርስባት ተወለደ እንጂ።
በባሕርየ መለኮቱ ጽድቅ እንጂ ኃጢአት፣ ሕያውነት እንጂ መዋቲነት የማይስማማው አምላክ እናት ትሆነው ዘንድ ከሴቶች መካከል መርጦ፣ ትህትናን እንደ ዝናር አስታጥቆ፣ ንጽህናን እንደ አክሊል አቀዳጅቶ፣ ካዘጋጃት ከቅድስት እናቱ ነፍስና ሥጋን ነሣ፡፡ የነሣውንም ሥጋ በተዋህዶ ከባሕርየ መለኮቱ ጋር አንድ አደረገው። ሥጋን ተዋህዶ ስለተወለደ ግን በባሕርየ ሰብእ ፀንቶ የነበረ መርገመ ሥጋ አላገኘውም፤ ድንግልም ኃጢአተ አበው የሚቆራኘው ተራ ሰውን የወለደች አይደለችም፡፡ የዚህ ዓለም ርኲሰት እንዳያገኛት ከእናቷ ማኅፀን ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ የጠበቃት ንጽህት እንደመሆኗ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሳለው ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ተብሎ የሚመሰገን የቅድስናው መጠን የንጽህናው ልክ የማይሰፈር የማይለካ ፍጹም ጌታን ወለደች እንጂ።
ቅዱስ ዲዮናስዮስ በሃይማኖተ አበው 101÷14 “አምላክን የወለደች አደፍ ጉድፍ የሌለባት ንጽህት በሆነች በድንግልማርያም ማኅፀን አደረ” መሆኗን ይነግረናል፡፡ ሌላው ታላቅ አባት ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ በዚሁ መጽሐፍ 35÷12 “መጀመሪያ የሌለው እርሱ አደፍ ጉድፍ የሌለባት ንጽህት ከሆነች ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም የነሣውን መገኛ ያለውን የሥጋ ባሕርይ ተዋሀደ” ይለናል፡፡ ከድንግል የተወለደ ክርስቶስ ኢየሱስ በሰው የተፈረደውን መከራ ተቀብሎ ሰውን ለማዳን ሰው ቢሆንም ቅሉ ዕድፈት ርኲሰት ያላገኘው ንጹህ ቅዱስ እንደሆነ አምላክን የወለደች ቅድስት ድንግል ማርያምም እድፈት ርኲሰት የሌለባት ንጽህት ቅድስት መሆኗን እንረዳለን። ይህን ንጽህናዋን የተረዱ ገዳማውያን ዘወትር በውዳሴዋና በቅዳሴዋ ሰዓሊ ለነ ቅድስት ይሏታል፡፡ ገዳማቸውን ሰንደግፍ በዓታቸውን ስናጸና በረከቷ ያድርብናል፡፡
ድጋፍ ለማድረግ:- ሙትአንሳ ማር ቅዱሰ ሚካኤል አንድነት ገዳም
ኢትዮጲያ ንግድ ባንክ
1000442598391
ወይም
አቢሲኒያ ባንክ
141029444
የገዳሙ ስልክ ቁጥር:-0918077957 ወይም 0938644444
1 year ago