Logo
FastMereja
400 የሚደርሱ የውጭ ሀገር ዜጎች የኢትዮጵያን ፓስፖርት ለማግኘት ሲሞክሩ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገለጸ

በ2017 በጀት ዓመት ከ3 ሺሕ 800 በላይ ሕገ-ወጥ ሰነድ ይዘው ፓስፖርት ለማግኘት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሰዎች መያዛቸውን የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት አስታውቋል፡፡

“ከእነዚህም ውስጥም ወደ 400 የሚጠጉት ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ የጎረቤት ሀገራት እና የሌሎችም አፍሪካ ሀገራት ዜጎች ናቸው” ሲሉ በአገልግሎቱ የፓስፖርት አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ ታደሰ ተናግረዋል፡፡

“በሦስት መልኩ የሚመጡ የሰነድ ማጭበርበሮች አሉ” ያሉት ዳይሬክተሩ፤ እነዚህም መታወቂያ እና የልደት ካርድን በተጭበረበረ መንገድ ማውጣት፣ ፈፅሞ ሀሰተኛ የሆነ መረጃ ይዞ መገኘት እና የኢትዮጵያ ዜጋ ሳይሆኑ የኢትዮጵያን ፓስፖርትን ለመያዝ መሞከር መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

“በዚህም በቀን በትንሹ ከ6 ያላነሱ ሰዎች በተጠቀሱት የማጭበርበር ወንጀሎች ተይዘው ለሕግ ክፍል ይቀርባሉ” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አንዳንድ ጊዜ ከኢሚግሬሽን አልፈው አየር መንገድ ላይ የሚያዙበት ሁኔታ መኖሩን የገለጹም ሲሆን፤ “የሁለት ሀገር ፓስፖርት ይዘው የሚገኙት ሰዎች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደልም” ብለዋል፡፡

የኤርትራ፣ የሶማሌላንድ ዜጎች እና ወታደሮች እንዲሁም ከሌሎች የሶማሊያ አካባቢዎች የመጡ ዜጎችና ናይጀሪያውያን በሕገ-ወጥ ድርጊቱ ሲሳተፉ ተይዘዋል ተብሏል፡፡

ከሕገ-ወጥ ስደት ጋር በተያያዘም በሕጋዊ መንገድ ፓስፖርት ከወሰዱ ዜጎች መካከል ከግማሽ በታቹ ከሀገር ለመውጣት ሕጋዊ መንገድ እንደሚጠቀም ተገልጿል፡፡

በ2017 ዓም 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ፓስፖርት መስጠት ተችሏል የተባለ ሲሆን፤ በ2018 ዓ.ም 4 ሚሊየን ፓስፖርት ለመስጠት መታቀዱም ነው የተገለጸው፡፡

ለዚህ የሚያግዙ 11 አዳዲስ ቅርንጫፎችን ለመክፈት ዝግጅት መጠናቀቁን የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ያስታወቀ ሲሆን፤ በክልሎችም ከወረፋ ጋር በተያያዘ የሚነሳውን ችግር ለማስቀረት ሥራ እየተሰራ ነው ተብሏል፡፡

1 year ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.