Logo
AHADU RADIO FM 94.3
በአዲስ አበባ በ 3 ወራት ውስጥ በአፈጻጸም ጉድለትና በብልሹ አሰራር 185 ሰዎች ተጠያቂ መደረጋቸው ተገለጸ

‎ጥቅምት 01ቀን 2019 ዓ.ም. (አሐዱ ሬድዮ) በአዲስ አበባ በ 3 ወራት ውስጥ በተከናወነው የስራ አፈጻጸም ግምገማ ከአፈጻጸም ጉድለት እና ከብልሹ አሰራር ጋር በተያያዘ 185 የሚሆኑ ግለሰቦች ላይ ጥብቅ እርምጃ መወሰዱን የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አበቤ አስታወቁ።

ከንቲባዋ የከተማ አስተዳደሩን የሩብ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንዳገለጹት ከዚህ ቀደም በከተማዋ "ጥሩ ሰው መባል በቂ የሚሆንበት" እና የአፈጻጸም ጉድለት እንደ ጥፋት የማይጠየቅበት አሰራር ነበር።

አሁን ግን ይህንን አዝማሚያ በመለወጥ በተደረገው ርብርብ ወደ 95 የሚሆኑ ሰዎች ከአፈጻጸም ጉድለት ጋር በተያያዘ ከቦታ መነሳት ፣ ማስጠንቀቂያ መስጠትንና ከኃላፊነት እንዲገለሉ ማድረግን ጨምሮ የተለያዩ እርምጃዎች ተወስደውባቸዋል።

በተመሳሳይ ከብልሹ አሰራርና ከሙስና ጋር በተያያዘ ከ90 በላይ የሚሆኑ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ፣ ሰራተኞች እና ተገልጋዮች በህግ ተጠያቂ መደረጋቸውን ከንቲባዋ ጠቁመዋል።

ከቦታ ታነሳላችሁ እንጂ አትጠይቁም" የሚል ወቀሳ ከህዝብ እንዳይነሳ ማን ፣ የት እና እንዴት ተጠያቂ እንደሆነ የሚያሳዩ ዝርዝር መረጃዎች ለህዝብ ግልጽ መደረግ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

በፋሲል አረጋይ

#አሐዱ_ሬዲዮ_94
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
14 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.