Logo
AHADU RADIO FM 94.3
የካሽ ሬጂስተር እና የተነጣጠሉ መሣሪያዎችን የአሠራር ፈተና የሚቀርፈው ንብተራ-ደረሰኝ ዲጂታል የክፍያ ደረሰኝ አገልግሎት በይፋ ሥራ ጀመረ

መስከረም 30 ቀን 2019 ዓ.ም. (አሐዱ ሬድዮ) ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ከፕራይም ኦል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኅበር ጋር በመተባበር፣ በዘርፉ የመጀመሪያ የሆነውን ንብተራ-ደረሰኝ የተሰኘ የተቀናጀ የዲጂታል ክፍያና የኤሌክትሮኒክስ ደረሰኝ አገልግሎት መስከረም 29 ቀን 2019 ዓ.ም. በትናትናው እለት በባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት በይፋ አስጀምሯል።

በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የሪቴይልና ኤስኤምኢ ባንኪንግ ዋና ሀላፊ አቶ ሙሉቀን ደምሴ የንብተራ-ደረሰኝ አገልግሎት ጊዜ ያለፈባቸውንና እርስ በእርስ የማይገናኙ የሽያጭ መመዝገቢያ ካሽ ሬጂስተሮችን በአንድ እጅ ብቻ በሚያዝ ዘመናዊ ስማርት ፖስ በመተካት፣ ነጋዴዎች ለደንበኞቻቸው የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲሰጡ ያስችላቸዋል ብለዋል።

አክለውም፣ ቴክኖሎጂው በገቢዎች ሚኒስቴር ዕውቅና የተሰጠውን የፕራይም ኦል ትሬዲንግ የኤሌክትሮኒክስ ደረሰኝ እና የድርጅት ሀብት አስተዳደር ሥርዓት ከባንኩ የዲጂታል መሠረተ ልማት ጋር በማቀናጀት፣ በአንድ ነጻ ስማርት ፖስ አማካኝነት የኤሌክትሮኒክስ ደረሰኝ ለማውጣት፣ የክፍያና የንግድ ሥርዓትን ለማዘመን የሚያስችል አስተማማኝ አሠራር መሆኑን ገልፀዋል።

የፕራይም ኦል ትሬዲንግ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ውብሸት አዝመራው በበኩላቸው፤ ንብተራ-ደረሰኝ ነጋዴዎች በርካታና የተለያዩ መሣሪያዎችን በመጠቀም ሲሰጡ የነበረውን ኋላቀር አገልግሎት በማስቀረት፣ በንግዱ ዘርፍ ሲስተዋሉ የነበሩትን የአሠራር ፈተናዎች በዘላቂነት ለመፍታት እንደሚያስችል ተናግረዋል።

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በንብተራ ዬዲጂታል የባንክ አገልግሎት ስር በርካታ መተግበሪያዎችን በማካተት፣ ለኅብረተሰቡ ዘመናዊና የተቀላጠፉ የክፍያ አማራጮችን እያቀረበ እንደሚገኝ ተገልጿል።

#አሐዱ_ሬዲዮ_94 .3
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ Photo
1 day ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.