Logo
FBC
ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረገ ለውጥ እና መሻሻል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ፣ የመሰረተ ልማት እና የማህበራዊ ዘርፎች ለውጥና መሻሻል የዜጎችን የእለት ተለት ህይወት በበርካታ መንገድ እየቀየረ ይገኛል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ7ኛ የስራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የሚመራውን መሠረታዊ እሳቤ በዝርዝር አስረድተዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ ጥቅም፣ ለውጥ እና መሻሻል እያንዳንዱን ዜጋ የማይነካ ከሆነ ዋጋ የለውም ብለዋል።

ይህ ፍልስፍና ባለፉት ጊዜያት የተመዘገቡ ስኬቶች መለኪያ ከመሆኑም በላይ ለአዲሱ የመደመር መንግሥት አቅጣጫ ጠቋሚ ሆኖ ያገለግላል።

የማክሮኢኮኖሚ ስኬት አኃዞችና የታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ትርጉም የሚያገኙት በዜጎች የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ተጨባጭ መሻሻል ማምጣት ሲችሉ ብቻ ነው። በሀገሪቱ የሚታዩ ዋና ዋና የእድገት መለኪያዎች በእያንዳንዱ ዜጋ የእለት እንቅስቃሴ ላይ በጉልህ ለውጥ እያመጡ ይገኛሉ፡፡

ከነዚህ መካከል ጥቂቶቹን እንመልከት፡-

በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች የተካሄደው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት የከተሞችን ገጽታ በመቀየር የቱሪስት ፍሰትን ከመጨመር ባሻገር የነዋሪዎችን የአኗኗር ዘይቤ በእጅጉ አሻሽሏል።

ለሕዝብ ክፍት የሆኑ አረንጓዴ ቦታዎችን፣ የጽዳትና የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓቶችን አለማምዷል፤ እንዲሁም ደህንነቱ የተጠበቀ የእግረኛ መንገድና የመሰረተ ልማት ዝርጋታን አስፋፍቷል።

በትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራሞችና በትምህርት ቤቶች ግንባታ ላይ የተደረጉ ኢንቨስትመንቶች አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ቤተሰቦች የኑሮ ጫና በማቃለል፣ የእድገቱ ፍሬዎች ጠንካራ፣ ጤናማና ባለሙያ ትውልድ እንዲገነቡ እያደረጉ ነው።

በክልሎች የጤና ተቋማት ቁጥር መጨመር እና ዘመናዊ የጤና መሰረተ ልማቶች መስፋፋት የዜጎችን ጤንነት ለማስጠበቅ እንዲሁም ፍትሀዊ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እገዛ አድርጓል።

የስንዴ ሰብል ልማት፣ የኩታገጠም እርሻና የመስኖ ልማት የግብርና ምርታማነትን በመጨመራቸው አርሶ አደሮች ከራስ አልፎ ለገበያ የሚሆን ምርት በማስገኘት፣ የቤተሰብ ገቢያቸውን ማሳደግና የምግብ ዋስትናን ማጠናከር ችለዋል።

የከተማ ግብርና፣ የመስኖ ልማት እና የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ በተጨማሪ ለዜጎች የሥራ እድልና ለአካባቢ ጥበቃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

በታዳሽ ኃይል፣ በንጹህ የመጠጥ ውሃና በዲጂታል ትስስር ላይ የተደረጉ ኢንቨስትመንቶች በከተማና በገጠር መካከል ያለውን ልዩነት እያጠበቡ ይገኛሉ።

እንደ ቴሌብር እና ፋይዳ (የዲጂታል መታወቂያ) ያሉ የቴክኖሎጂ ስርአቶች የባንክ፣ የክፍያ እና የመንግሥት አገልግሎቶችን በቀላሉ እና በፍጥነት ለማግኘት አስችለዋል፤ የንግድ እንቅስቃሴን ቀልጣፋ አድርገዋል።

የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲሁም የመጠጥ ውሀ ተደራሽነት መስፋፋት ለአነስተኛ ነጋዴዎችና ለገጠሩ ማህበረሰብ አዳዲስ የኢኮኖሚ እድገት ዕድሎችን ከፍቷል።

በእነዚህ እና ሌሎችም የሚገለጸው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ፣ የመሰረተ ልማት እና የማህበራዊ ዘርፎች ለውጥና መሻሻል የዜጎችን የእለት ተለት ህይወት በበርካታ መንገድ እየቀየረ ይገኛል፡፡
#የመደመር_መንግሥት

በምሕረት ደምሴ

2 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.