Logo
SeledaPost
የህወሓት ታጣቂዎች “ከባድ የጦር መሣሪያዎችን ወደ ኤርትራ ድንበር እያሸሹ” መሆኑን ጄነራል ደርቤ መኩሪያ ገለጹ

በትግራይ ክልል ዳግም ባገረሸው ጦርነት፤ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ(ህወሓት)፣ “ከባድ እና ሜካናይዝድ የጦር መሣሪያዎችን ወደ ኤርትራ ድንበር እያሸሸ” መሆኑን የብሔራዊ ተሃድሶ ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዴር ጄነራል ደርቤ መኩሪያ ተናገሩ።

ምክትል ኮሚሽነሩ በሰጡት መግለጫ፤ የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሰራዊት ባካሄደው “የመልሶ ማጥቃት እርምጃ” በርካታ የአካባቢዎችን ነፃ ማውጣቱን ተከትሎ፣ የህወሓት ታጣቂዎች ተበትነው ሜካናይዝድና ከባድ መሳሪያዎችን ወደ ኤርትራ ድንበር የማሸሽ እና የመሸሸግ ተግባር ላይ እንደሚገኙ አረጋግጠዋል።

ብርጋዴር ጄነራል ደርቤ ከ30 ደቂቃዎች በላይ በወሰደው መግለጫቸው እንዳመለከቱት፣ ይህ አዲስ የጦርነት እንቅስቃሴ በሀገር ውስጥ ባሉ ተቃዋሚ ኃይሎች እና በውጭ ሀገራት መካከል በተፈጠረ የተቀናጀ ስትራቴጂካዊ ትብብር የሚመራ ነው።

“ጽንፈኛ” እያሉ የጠሩት የህወሓት ቡድን በሀገር ውስጥ ከሚንቀሳቀሱት የፋኖ ታጣቂዎች እና ራሱን የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ብሎ ይጠራል ካሉትና “አሸባሪ ቡድን” ሲሉ ከገለጹት ታጣቂ ጋር ቅንጅት መፍጠሩን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ቀጣናዊ ደህንነትን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፣ የኤርትራ (ሻዕቢያ) መንግሥት ትግራይ ውስጥ ዘላቂ መረጋጋት እንዳይኖር የማዳከም ፍላጎት ይዞ ሂደቱን ከመደገፉ ባሻገር፣ በሱዳኑ ፕሬዝዳንት በጄነራል አብዱል ፋታህ አል -ቡርሃን የሚመራው ያሉት ቡድን እና የግብፅ መንግሥት የኢትዮጵያን የውስጥ ተጋላጭነት በመጠቀም ሀገሪቱን ለማዳከም “አደገኛ ጥምረት መፍጠራቸውን” አስረድተዋል።

የህወሓት አመራሮች የሚከተሉት የጦርነት ስልት “እጅግ ኋላቀር እና ከ30 ዓመታት በፊት ይተገበር የነበረ” ሲሉ ምክትል ኮሚሽነሩ ነቅፈውታል።

ቡድኑ በርካታ የትግራይ ወጣቶችን ያለፍላጎታቸው በማሰለፍ፣ ከፊት ታጣቂዎችን እና ከኋላ ደግሞ የሚያስገድድ “ግብረ-ኃይል” በማስቀመጥ ወጣቱን የመውጫ ቀዳዳ እንዳያገኝ አድርጎ በሁለቱ መካከል በማድረግ “የሰው ማዕበል” (ሂዩውማን ዌቭ) ስልት እየተጠቀመ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ለዲዲአር(ትጥቅ መፍታት፣ መበተንና መልሶ ማቋቋም) ተሃድሶ ፕሮግራም የተዘጋጁ እና አዳዲስ የተመለመሉ ወጣቶች በአስገዳጅ አዋጅ እና ህግ ተጠቅመው ወደ ጦርነቱ እንዲገቡ መደረጋቸውን የጠቆሙት ብርጋዴር ጄነራል ደርቤ፣ ከፍተኛ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አመራሩ ራሳቸው ከሩቅ ሆነው ጦርነቱን እንደሚመሩና የትግራይ ህዝብና ወጣቱ ጦርነቱን እንደሚቃወሙት ተናግረዋል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት ያለው የአየር እና የቴክኖሎጂ የበላይነት ከፍተኛ ቢሆንም፣ ተገድደው ወደ ጦርነቱ የገቡ ወጣቶችን ሕይወት ለማትረፍ ሲባል እርምጃዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ እየተካሄዱ እንደሚገኙ ተገልጻል።

የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት የመቀበል እና መልሶ የማቋቋም ተልዕኮውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን በመግለጽ፣ የታጠቁ ኃይሎችና አመራሮች የተዘጋጁትን የቅበላ ማዕከላት (እንደ ሽሬ፣ መቀሌ፣ አድዋ፣ ማይጨው እና አዲግራት ያሉ) በመጠቀም እጃቸውን እንዲሰጡ እና የቀረበውን የመጨረሻ የሰላም እድል እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።

Seledadotio
Seledadotio
2 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.