Logo
AHADU RADIO FM 94.3
በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ወደ ተሃድሶ መግባት እንዲችሉ በተለያዩ አካባቢዎች የቅበላ ማዕከላት ተዘጋጅተዋል። ብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን

መስከረም 30 ቀን 2019 ዓ.ም. (አሐዱ ሬድዮ) በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ወደ ተሃድሶ መግባት እንዲችሉ በተለያዩ አካባቢዎች የቅበላ ማዕከላት መዘጋጀታቸውን ብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን አስታወቀ።

የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዴር ጄኔራል ደርቤ መኩሪያው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በአሁኑ ወቅት በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች መንግስት ወደ አዘጋጀላቸው ማዕከላት ለመግባት ጥሪውን እየተጠባበቁ መሆኑ ታውቋል።

መንግሥት ወደ ሰላም አማራጭ የሚመጣ ማንኛውም አካል በተሃድሶ ሂደትን አልፎ፣ ወደ ማህበረሰቡ በመቀላቀል የተረጋጋ ሕይወት እንዲመራ ያለውን ጽኑ ፍላጎት ገልጸዋል፡፡

መከላከያ ሠራዊትም ወደ ሰላም የሚመጣውን ኃይል በአግባቡ የመቀበል፣ የማስተናገድ እና ወደ ብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን ማዕከላት የማድረስ ሥራውን በተደራጀ መንገድ እየተገበረ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

ኮሚሽኑ ታጣቂዎቹና አመራሮቻቸው በተሐድሶ ሂደት እንዲያልፉ የመቀበያ ማዕከላትን በዞኖችንና ከተሞችን ማዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡

በዚህም ደቡባዊ ዞን ራያ አካባቢ ማይጨው እና መሆኒ ከተሞች፤ ደቡብ ምስራቅ ዞን መቀሌና አካባቢው በመቀሌ ከተማ በሚገኘው የሰሜን እዝ ጠቅላይ መምሪያ፤ ምስራቃዊ ዞን በአዲግራት እና በውቅሮ ከተሞች የመቀበያ ማዕከላት መዘጋጀታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በተጨማሪም በማዕከላዊ ዞን በአድዋ፣ አክሱም እና አቢዓዲ ከተሞች እንዲሁም በሰሜን ምዕራብ ዞን በሽሬ ከተማ በሚገኘው የቀድሞው ማዕከላዊ እዝ ጠቅላይ መምሪያ ላይ የመቀበያ ማዕከል መዘጋጀቱን ነው የገለፁት።

የመከላከያ ሠራዊት አባለት ታጣቂዎችን ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውን አንስተው ታጣቂዎች በእጃቸው የሚገኘውን ትጥቅና ወታደራዊ ቁሳቁስ በማስረከብ ወደ ተዘጋጀላቸው የተሃድሶ ማዕከላት እንደሚገቡ አስታውቀዋል።

#አሐዱ_ሬዲዮ_94
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ Photo
1 day ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.