Logo
ዳጉ-ጆርናል/Dagu-Journal
ሎተሪ ደርሶናል በማለት የማታለል ወንጀል የፈፀሙ ተጠርጣሪዎች እጅ ከፍንጅ ተያዙ

አርሴማ ማስረሻ፣ ታደሰ ነሪ እና ዮሴፍ ተሾመ የተባሉት ተጠርጣሪዎች የማታለል ወንጀሉን ፈፅመው በቁጥጥር ስር የዋሉት በኮልፌ ቀራንዮ ክ/ከተማ ወረዳ 6 ቤቴል አካባቢ ነው።

ተጠርጣሪዎቹ በተከራዩት ቪቲዝ መኪና በመንቀሳቀስ የግል ተበዳይ የቀበሌ መታወቂያ ለማሳደስ በአዲስ ከተማ ክ/ከተማ ወረዳ 12 አስተዳደር በሚሄዱበት አጋጣሚ ያገኟቸዋል።

ታደሰ ነሪ የተባለው ግለሰብ ቤትና መኪና የሚያስገኝ ሎተሪ ቢደርሰውም በቅርቡ ከክፍለ ሃገር ስለመጣ መታወቂያ እንደሌለውና ጉዳዩን ለማስጨረስ የግል ተበዳይን እርዳታ እንደሚፈልግ በመናገር አታለው መኪና ውስጥ ያስገቧቸዋል።

ግለሰቦቹ ለ3 ሠዓታት ያህል የግል ተበዳይን በተለያዩ ቦታዎች ሲያዞሯቸውና ሲያንገላቷቸው ከቆዩ በኃላ የተለያዩ የማሳመኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ለጉዳዩ ማስጨረሻ በሚል ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክና እናት ባንክ 100 ሺህ ብር አውጥተው ይሰጧቸዋል።

በተጨማሪም ቤቴል ወረዳ 6 አካባቢ ከሚገኝ የአንድ ግለሰብ ህንፃ አጠገብ ሲደርሱ ፣ የወርቅ ጌጣጌጥና ሞባይል ስልክ ይዞ መግባት እንደማይቻል፤ በመግለፅ እስከሚመጡ ድረስ የግል ተበዳይ ንብረት በእነሱ እጅ እንዲቆይ ያደርጋሉ።

የግል ተበዳይም 220 ሺህ ብር የሚያወጣ 11 ግራም የአንገት ሃብልና የጆሮ ጌጥ ወርቅ እንዲሁም 17 ሺህ ብር የሚገመት ሳምሰንግ ሞባይል ስልክ በአጠቃላይ 337 ሺህ ብር ግምት ያለው ንብረት ለተጠርጣሪዎቹ አስረክበው ቤትና መኪና የደረሰን ሎተሪ በሚል በትንሽ ካኪ ወረቀት ውስጥ የታሸገ 75 ሺህ ብር የሚል ፅሁፍ ያለው የተፋቀ የፈጣን ሎተሪ ወረቀት ሰጥተዋቸው ከመኪናው እንዲወርዱ ካደረጉ በኃላ የግል ተበዳይን ንብረት ይዘው ለማምለጥ ሲሞክሩ በፖሊስ ተይዘዋል ።

#ዳጉ_ጆርናል
2 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.