Logo
YenetaTube
ቤትና መኪና የሚያስገኝ ሎተሪ ደርሶናል በማለት የማታለል ወንጀል የፈፀሙ 3 ተጠርጣሪዎች እጅ ከፍንጅ ተያዙ።

አርሴማ ማስረሻ፣ ታደሰ ነሪ እና ዮሴፍ ተሾመ የተባሉት ተጠርጣሪዎች የማታለል ወንጀሉን ፈፅመው በቁጥጥር ስር የዋሉት በኮልፌ ቀራንዮ ክ/ከተማ ወረዳ 6 ቤቴል አካባቢ ነው።

ተጠርጣሪዎቹ ወንጀሉን ለመፈፀም አስበው በተከራዩት የሰሌዳ ቁጥር ኮድ3A-73299 አ.አ የሆነ ቪቲዝ መኪና እየተንቀሳቀሱ እያለ የግል ተበዳይ የቀበሌ መታወቂያ ለማሳደስ በአዲስ ከተማ ክ/ከተማ ወረዳ 12 አስተዳደር በሚሄዱበት አጋጣሚ ያገኟቸዋል።

ከሦስቱ ተጠርጣሪዎች መካከል ታደሰ ነሪ የተባለው ግለሰብ ቤትና መኪና የሚያስገኝ ሎተሪ ቢደርሰውም በቅርቡ ከክፍለ ሃገር ስለመጣ የአዲስ አበባ ከተማ መታወቂያ እንደሌለውና ጉዳዩን ለማስጨረስ የግል ተበዳይን እርዳታ እንደሚፈልግ በመናገር አታለው መኪና ውስጥ ያስገቧቸዋል።

ግለሰቦቹ ለ3 ሠዓታት ያህል የግል ተበዳይን በተለያዩ ቦታዎች ሲያዞሯቸውና ሲያንገላቷቸው ከቆዩ በኃላ የተለያዩ የማሳመኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ለጉዳዩ ማስጨረሻ በሚል ማታለያ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክና እናት ባንክ 100 ሺህ ብር አውጥተው ለተጠርጣሪዎቹ ይሰጧቸዋል።

በዚህ የማታለል ወንጀል ያላበቃው የተጠርጣሪዎቹ ተግባር ቤቴል ወረዳ 6 አካባቢ ከሚገኝ የአንድ ግለሰብ ህንፃ አጠገብ ሲደርሱ በሎተሪ የደረሳቸውን ቤትና መኪና መውሰድ የሚችሉት በዚህ ህንፃ ቢሮ ውስጥ መሆኑንና ገብተው እንዲያስጨርሱላቸው ካሳመኗቸው በኃላ ቢሮ ውስጥ ሲገቡ የወርቅ ጌጣጌጥና ሞባይል ስልክ ይዞ መግባት እንደማይቻል፤ ጉዳዩን አስጨርሰው እስከሚመጡ ድረስ የግል ተበዳይ ንብረት በእነሱ እጅ እንዲቆይ ያደርጋሉ።

የግል ተበዳይም 220 ሺህ ብር የሚያወጣ 11 ግራም የአንገት ሃብልና የጆሮ ጌጥ ወርቅ እንዲሁም 17 ሺህ ብር የሚገመት ሳምሰንግ ሞባይል ስልክ በአጠቃላይ 337 ሺህ ብር ግምት ያለው ንብረት ለተጠርጣሪዎቹ አስረክበው ቤትና መኪና የደረሰን ሎተሪ በሚል በትንሽ ካኪ ወረቀት ውስጥ የታሸገ 75 ሺህ ብር የሚል ፅሁፍ ያለው የተፋቀ የፈጣን ሎተሪ ወረቀት ሰጥተዋቸው ከመኪናው እንዲወርዱ ካደረጉ በኃላ የግል ተበዳይን ንብረት ይዘው ለማምለጥ ሲሞክሩ በፖሊስ አባላትና ህብረተሰቡ ትብብር በቁጥጥር ስር መዋላቸውን በኮልፌ ቀራንዮ ክ/ከተማ ፖሊስ ዋና መምሪያ የቤቴል አካባቢ ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል።

ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅትም ሴት ተጠርጣሪዋ የማታለል ወንጀሉን ለመፈፀም በአርቴፊሻል ፀጉር እራሷን እንደምትቀያይር የግል ተበዳይ የሰጡት ቃልና የምርመራ መዝገቡ እንደሚያስረዳ ፖሊስ መምሪያው ገልጿል።

ወንጀል ፈፃሚዎች የተለያዩ የማታለያ ዘዴዎችን በመጠቀምና የሰዎችን እንቅስቃሴ በመከታተል መሰል ወንጀል ሊፈፅሙ ስለሚችሉ ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ያሳሰበው የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ወንጀል ከተፈፀመም በአፋጣኝ ለፖሊስ ማሳወቅ ተገቢ መሆኑን በመልዕክቱ አስተላልፏል።

8 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.