Logo
AHADU RADIO FM 94.3
ከ4.2 ሚሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የወተት ጥራት መመርመሪያ መሳሪዎች በ11 ክፍለ ከተሞች መሰራጨት ጀመረ

መስከረም 29 ቀን 2019 ዓ.ም. (አሐዱ ሬድዮ) በአዲስ አበባ ለህብረተሰቡ የሚቀርበውን ወተት ጥራት እና ደህንነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ከ4.2 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ዘመናዊ መመርመሪያ መሳሪያዎች በ11ዱም ክፍለ ከተሞች መሰራጨት መጀመሩን የአዲስ አበባ አርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን አስታውቋል።

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ዶክተር ጸጋ ለማ ለአሐዱ ሬዲዮ እንደገለጹት ወተትን ከባዕድ ነገር ጋር ተቀላቅሎ ለገበያ ሲቀርብ በዓይን አይቶ ለመለየት እጅግ አስቸጋሪ በመሆኑ ቴክኖሎጂን መጠቀም የግድ ይላል።

በመሆኑም ከጥርጣሬ የጸዳ እና ውጤታማ የሆነ የቁጥጥር ስራ ለመስራት የሚያስችሉ እና ከፍተኛ ካፒታል የሚጠይቁ ዘመናዊ መፈተሻ መሳሪያዎችን ለሁሉም ክፍለ ከተሞች የማከፋፈል ስራ ተጀምሯል።

የመሳሪያዎቹ አቅርቦት SNV ከተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በተደረገ ትብብር የተገኘ መሆኑን የገለጹት ምክትል ኮሚሽነሩ ከቁሳቁስ አቅርቦቱ ጎን ለጎን የቁጥጥር ስራውን የሚያከናውኑ ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና መውሰዳቸውን ተናግረዋል።

በዚህም መሰረት ከሁሉም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ 22 ተቆጣጣሪዎች በዘርፉ በታወቁ ሀገር አቀፍ አሰልጣኞች አማካኝነት ለአምስት ተከታታይ ቀናት ተግባር ተኮር ስልጠና ተሰጥቷቸዋል።

ከዚህ ቀደም የወተትን ደህንነት እና ጥራት ነባራዊ ሁኔታ ለማጥናት ከተለያዩ የከተማው እና የፌደራል ባለድርሻ አካላት ጋር የዳሰሳ ጥናት መደረጉን ያስታወሱት ዶክተር ጸጋ በጥናቱ ላይ በመመስረትም የወተት ጥራትን የሚቆጣጠር የህግ ማዕቀፍ የማዘጋጀት ስራ መሰራቱን አብራርተዋል።

በአሁኑ ሰዓትም በሰለጠነ የሰው ሀይል እና በተሟላ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ የከተማዋን የወተት ጥራትና ደህንነት የማስጠበቅ ስራን በስፋት ለመጀመር የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ መሆኑ ተገልጿል።

በፋሲል አረጋይ

#አሐዱ_ሬዲዮ_94 .3
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ Photo
20 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.