Logo
EBC
ከቤት ደጃፍ እስከ አፍሪካ ክብር፤ የኢትዮጵያ ቡና ዓለም አቀፍ ከፍታ
****************

“ኑ ቡና ጠጡ፣ ቡና ፈልቷል” የሚለው ጥሪ በኢትዮጵያውያን የዘወትር ሕይወት ውስጥ ትልቅ የፍቅርና የእንግዳ ተቀባይነት ግብዣ ነው።

በዚሁ የቡና አፈላል ሥነ-ሥርዓት ወቅት ማኅበራዊ ውይይቶች ይካሄዳሉ፤ ጥልቅ ትስስር ይፈጠራል።

የኢትዮጵያዊነት አንዱ መገለጫ የሆነው የቡና ስነ ስርዓት ከእርሻ ማሳዎች እስከ ሲኒያችን ድረስ የአርሶ አደሩ እጅ ቤተሰብንና ማኅበረሰብን የሚደግፍ ታላቅ እሴት ነው።

ይህ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር የመጣ የቡና ባህል በቤትና በማኅበረሰብ ደረጃ ብቻ ተወሰኖ አልቀረም።

ዛሬ የኢትዮጵያ ቡና ሌላ አዲስ የክብር ገጽታውን ለአፍሪካና ለዓለም አሳይቷል።

በአንድ ቀን 10 ሺህ ሲኒ ቡና በአንድ ሥፍራ በማቅረብ፣ ባህላዊ የቡና አፈላል ሥርዓቱ በአፍሪካ የድንቃድንቅ መዝገብ ውስጥ ዕውቅና አግኝቷል።

በመሆኑም “ኑ ቡና ጠጡ” የሚለው ጥሪ ከቤት ደጃፍ አልፎ በአህጉራዊ የክብር መዝገብ ውስጥ በመግባት፣ ከ“ኑ ቡና ጠጡ” ወደ “የኢትዮጵያን ባህልና አብሮነት ይዩ” ወደሚል ሰፊ አህጉራዊ ጥሪ ተሸጋግሯል።

ኢትዮጵያ የአረቢካ ቡና መገኛ እና የአፍሪካ ቀዳሚ ቡና አምራች ሀገር ስትሆን፣ የመጀመሪያው የቡና ፍሬ ተለቅሞና ተሰብስቦ ለዓለም የተበረከተው እዚሁ በኢትዮጵያ ምድር ነው።

ሀገራችን በ2018 በጀት ዓመት ከቡና ወጪ ንግድ ከ3.1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማስመዝገብ ችላለች።

ይህም ኢትዮጵያ ባለፉት 17 ዓመታት በአጠቃላይ ካገኘችው 3.3 ቢሊዮን ዶላር የገቢ መጠን ጋር የሚቀራረብ ነው።

በተጨማሪም በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች በሚተከሉበት የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር ውስጥ ሰፊውን ቁጥር የሚይዙት የቡና ችግኞች ናቸው።

ይህም ደኖችን መልሶ ለማቋቋም፣ ሥነ-ምህዳርን ለመጠበቅ እና የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስፈልገውን አየር ንብረት ለመፍጠር አስችሏል።

ከዚህ ዕድገት ጎን ለጎን ኢትዮጵያ የቡና በሽታን ለመለየትና ለማከም የሚያስችሉ አዳዲስ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ቴክኖሎጂዎችን እና ምርምሮችን በማሳደግ ላይ ትገኛለች።

በልዩ እሸቱ
#የመደመርመንግሥት
#ethiopia #ebc #medemer #ethiopiancoffee #coffeeculture

1 day ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.