Logo
Getu Temesgen
በወተት ምርትና ስርጭት ላይ የሚታዩ የጥራት ችግሮችን ለመቆጣጠር አዲስ ረቂቅ ደንብ እየተዘጋጀ ነው
#ethiopia | በወተት ምርት፣ አያያዝና ስርጭት ላይ የሚታዩ የጥራትና የንፅህና ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ያለመ ረቂቅ የሕግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑን የአዲስ አበባ አርሶ አደርና ከተማ ግብርና ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ በ2018 በጀት ዓመት ባካሄደው ጥናት ከወተት እርባታ ሼዶች እስከ ችርቻሮ መሸጫ ሱቆች ድረስ የንፅህና ጉድለቶች መኖራቸውን መለየቱን ገልጿል።

በእርባታ ቦታዎች አላቢዎች ተገቢውን የደንብ ልብስ አለመልበሳቸውና የንፅህና አጠባበቅ ክፍተቶች መኖራቸው በጥናቱ ከተለዩ ችግሮች መካከል ተጠቅሰዋል። በተጨማሪም ላሞች ሲታመሙ የሚሰጣቸው መድኃኒት ከሰውነታቸው ሙሉ በሙሉ ሳይወጣ ወተቱ ለገበያ የሚቀርብበት ሁኔታ መኖሩ ተመልክቷል።

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ዶክተር ጸጋ ለማ እንደገለጹት፣ ወተት ለማለብ፣ ለማጠራቀምና ለማጓጓዝ ተገቢውን የምግብ ደህንነት መስፈርት የማያሟሉ የፕላስቲክ ጀሪካኖች በስፋት እየተጠቀሙ ነው። ይህም ለማፅዳት አስቸጋሪ በመሆኑ በወተት ጥራትና ደህንነት ላይ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ጠቁመዋል።

ከዚህም በተጨማሪ፣ ወተት ውስጥ ውሃ በመጨመር ተፈጥሯዊ ይዘቱን የማዛባት ሕገወጥ ድርጊት በአንዳንድ አካላት እየተፈጸመ መሆኑን ምክትል ኮሚሽነሩ አመልክተዋል።

ኮሚሽኑ እነዚህን የምግብ ደህንነትን የሚጎዱ ተግባራት ለመቆጣጠር፣ ሕጋዊ እርምጃዎችን ለመውሰድና በወተት ምርት ሰንሰለት ውስጥ የሚታዩ ክፍተቶችን ለማስተካከል አዲስ ረቂቅ ደንብ አዘጋጅቶ ለማስጸደቅ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጿል።

ረቂቅ ደንቡ ጸድቆ ወደ ተግባር ሲገባ፣ ከእርባታ ጀምሮ እስከ ምርት ማጓጓዝ፣ ማከማቸትና ለሸማቾች ማቅረብ ድረስ ባለው የንግድ ሰንሰለት ውስጥ የጥራትና የንፅህና መስፈርቶችን ለማስጠበቅ አስፈላጊ ሚና እንደሚኖረው ተገልጿል።

ይህም ለህብረተሰቡ ጤናማ፣ ጥራቱ የተጠበቀና ደህንነቱ የተረጋገጠ ወተት እንዲደርስ እንደሚያግዝ ይጠበቃል።

ፋሲል አረጋይ — አሐዱ

12 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.