Logo
AHADU RADIO FM 94.3
በባብሌ ዝሆኖች መጠለያ የደረሰው ሕገ-ወጥ ሰፈራ በሰው እና እንስሳት ላይ አደጋ መደቀኑ ተገለጸ

👉ዝሆኖች የ4 ሰዎች ህይወት አጥፍተዋል ተብሏል

በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ በሚገኘው የባብሌ ዝሆኖች መጠለያ በደረሰ ሕገ-ወጥ ሰፈራ ምክንያት ዝሆኖች ከመኖሪያ ስፍራቸው ወጥተው በሰውና እንስሳት ላይ አደጋ መደቀናቸውን የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ለአሐዱ ሬድዮ አስታውቋል።

የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን መኮንን፣ "የመጠለያው ዋና የዝሆኖች መራቢያና ማረፊያ ስፍራ በሕገ-ወጥ ሰፋሪዎች በመያዙ ዝሆኖቹ ከመጠለያቸው ለመውጣት ተገደዋል" ብለዋል። በዚህም ምክንያት በተጠናቀቀው የ2018 በጀት ዓመት ወደ ምስራቅ ሐረርጌ አካባቢ በመግባታቸው የ4 ሰዎችን ሕይወት ማለፉን አብራርተዋል።

ችግሩን ለመፍታት በ2013 ዓ.ም. በተደረገ ጥረት በኦሮሚያ በኩል የነበሩ ከ760 በላይ አባወራዎችን ማስወጣት ቢቻልም፤ በሶማሌ ክልል በኩል ተመሳሳይ የተቀናጀ ሥራ ባለመሠራቱ ሰፋሪዎቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተመልሰው መግበታቸውን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

አክለውም፤ ሕገ-ወጥ ሰፈራውና ውጥረቱ በሰው ላይ ብቻ ሳይሆን በዝሆኖቹም ሕይወት ላይ አደጋ እያደረሰ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ይህንን ዘላቂ ችግር ለመፍታት የሁለቱም ክልሎች ከፍተኛ አመራሮችና ፕሬዝዳንቶች የጋራ እቅድ ነድፈው ወደ ሥራ መግባት እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል።

በወልደሐዋርያት ዘነበ

#አሐዱ_ሬዲዮ_94 .3
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
11 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.