Logo
YenetaTube
እንኳን ለመስቀል ደመራ በዓል አደረሳችሁ፤ አደረሰን🙏

መስቀል በብሉይ የወንጀለኞች መቅጫ ቢሆንም ለዓለም መዳኛነት መርጦታልና ትንቢት ሲነገርለት፣ በበርካታ ምሳሌዎች ሲገለጥ ኖሯል፡፡

የሰው ልጅ ራሱ አርአያ ትዕምርተ መስቀል ነው፡፡ ይስሐቅ ሊሰዋ ሲሔድ የተሸከመው እንጨት፣ ቅዱስ ያዕቆብ ያያት የወርቅ መሰላል፣ ባሕረ ኤርትራን የከፈለችው የሙሴ በትር፣ የነሐሱ እባብ የተሰቀለበት እንጨትና ሌሎች ምሳሌዎችን የትርጓሜ መምሕራን ይነግሩናል፡፡

ይህም ቅዱስ መስቀሉ ጌታችን ለሰው ልጅ ፍጹም ፍቅሩን ሲገልጽበት፣ ሥጋውን ሲቆረስበት፣ ደሙን ሲያፈስበት፣ በምክንያት እደሆነ ያሳየናል፡፡ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማያት ወርዶ፣ ከቅድስት ድንግል ማርያም በኅቱም ድንግልና ተወልዶ፣ በፈቃዱ መከራ መስቀልን ተቀብሎ፣ ከሰይጣን ባርነት፣ ከኃጢአት ቁራኝነትም አድኖናል:: ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙር 59÷4 "ለሚፈሩሕ ከቀስት ያመልጡ ዘንድ ምልክትን ሰጠሃቸው" በማለት መስቀሉን በትንቢት ይገልጸዋል፡፡

ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ዻውሎስ (በ1ኛ ቆሮ 1÷18 እና በገላ 6÷14) ስለ መስቀሉ አምልቶ አስፍቶ ጽፏል፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድም "ከነገር ሁሉ የሚበልጠው መስቀል ከጠላታችን ያደነናል" ይለናል፡፡ እኛም ለመስቀሉ የጸጋ ስግደት እንሰግዳለን፣ እናመሰግነዋለን፣ እናከብረዋለን፤ አምነን ከብረን እንኖራለን፡፡ አባቶቻችን በመስቀሉ ምርኩዝነት የኃጢአት ማዕበልን፣ ባሕረ እሳትን ተሻግረዋል፣ አጋንንትን ድል ነስተዋል፡፡ የክብር ባለቤት ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል ተአምራትን ሲያደርግ አይሁድ በምቀኝነት ለሦስት መቶ ዓመት ቀብረው አጥፍተውታል፡፡ በዚህም ምክንያት የጻድቁ የሮም ንጉስ የቆስጠንጢኖስ እናት ንግስት እሌኒ ልጇ ክርስቲያን ከሆነ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዳ መስቀሉን ልትፈልግ ለእግዚአብሄር ተስላ ነበር።

ልጇ አምኖ ሲጠመቅም ብዙ ሰራዊት አስከትላ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደች፡፡ ስለ ከበረው መስቀል የሚያስረዳት ግን አላገኘችም፡፡ የአይሁድ ወገን የሆነ አንድ ኪራኮስ የሚባል አረጋዊም አስራ ስታስጨንቀው የጎልጎታ ኮረብታ ላይ ተቀብሯል ተብሎ ሲነገር እንደሰማ ነገራት፡፡ አይሁድ የከበረ መስቀሉን በቀበሩበት ስፍራ ሦስት የቆሻሻ ተራሮች ነበሩና የትኛው ላይ እንደተቀበረ ለማወቅ መስከረም 16 ደመራ ደምራ ስታቃጥለው የእጣኑ ጢስ መስቀሉ ያለበትን ስፍራ አመለከታት፡፡ መስከረም 17 ቀንም ከሁለት መቶ ዓመት በላይ የተቀበረው መስቀል ቁፋሮው ተጀምሮ መጋቢት 10 ቀን ሶስት መስቀሎች ተገለጡ፤ ነገር ግን የክብር ባለቤት ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል የትኛው እንደሆነ አላወቁም ነበር።

በገቢረ ተአምራት ለመለየትም የሞተ ሰውም አመጡና መስቀሉን ሲያደርጉበት ተነሳ እሌኒም የክርስቶስ መስቀል እንደሆነ አውቃ ሰገደችለት የክርስቲያንም ወገኖች ሁሉ ሰገዱለት። ከዚህም በኃላ ለቅዱስ መስቀሉና የሚሆንና ሌሎችም አብያተ ክርስቲያናት አነፀች። ለበረከት እንዲሆናትም ጥቂት ወስዳ ወደ ሀገሯ ተመለሰች፡፡ በሮሙ ንጉስ በህርቃል ዘመን የፋርሱ ንጉስ መጥቶ ኢየሩሳሌምን አጠፋት የከበረ መስቀሉንም ይዞ ብዙ ሰዎችን ማርኮ ወደ አገሩ ተመለሰ። የሮም ንጉስ ህርቃልም ወደ ፋርስ ዘምቶ ድል ነሳቸው፤ የከበረ እፀ መስቀሉንም ጥቂት ለበረከት ወስዶ ወደ ኢየሩሳሌም መለሰው፡፡ የክርስትናው ዓለም ይህን እጸመስቀል ለአራት ሲከፋፈለው የእስክንድርያ ድርሻ በ15ኛ መቶ ክፍለ ዘመን በአፄ ዳዊት ወደ ሃገራችን መጥቶ በአፄ ዘርዓ ያዕቆብ አማካኝነት በግሸን ማርያም ደብረ ከርቤ ተቀምጧል፡፡ ገዳማውያንም በመስቀሉ ኃይል ዘወትር የጠላትን ኃይል ድል ይነሱበታልና ገዳማቸውን ስንደግፍ በዓታቸውን ስናጸና በረከታቸው ያድርብናል፡፡

ድጋፍ ለማድረግ፡- ቤተ ቅዱሳን ፈትለወርቅ ማርያም የእናቶች ገዳም፡-

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

1000766349227

ወይም

አቢሲንያ ባንክ

262281132

የገዳሙ ስልክ ቁጥር፡- 0944672222 ወይም 0916106921

12 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.