Logo
YenetaTube
"ጦርነት ሀገርን ከማደኅየትና ሕዝብን ለተደራራቢ መከራ ከመዳረግ በቀር ይህ ነው የሚባል ጥቅም የሌለው መሆኑን በመገንዘብ በዚህ የተሰለፉ ኃይሎች መስቀሉን (ሰላምን) ከመቅበር ወጥተው የመስቀሉን ዓላማ ሊፈጽሙ ይገባል" ብፁዕ አቡነ ሄኖክ ሊቀ ጳጳስ

"እስመ መስቀል ሞዓ ሞት ተሞዓ ኃይለ መስቀሉ አብርሃ፤ መስቀል ሞትን ድል አደረገ፤ የመስቀሉም ኃይል አበራ።"

የአሸናፊነት ምልክት፣ የመዳኛችን መንገድ፣ በብርሃን የሚመራንና የሕይወት መንገዳችን ነፀብራቅ ነው ቅዱስ መስቀሉ፤ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ "አንዱ ዛፍ የሞት ምክንያት እንደሆነ፣ ሌላው ዛፍ የሕይወት ምክንያት ሆነ” እንዳለ ወደሞት የወረድንበት እና የሰው ልጆች ታሪክ ብልሽት የጀመረበትን ሂደት የምናስታውሰው በዕፀ በለስ ነው፤ እነሆ የቀደሙት ሰዎች የእንጨት ፍሬ የሆነውን በልተው እንደሞቱ እና ልጅነትን እንዳጣን ሁሉ፤ ድንቅ የአባትነት ፍቅሩን የገለጸልን መድኃኔዓለም ክርስቶስም በወደቅንበት በኩል ማንሳትን የሚያውቅ አምላክ ነውና በእንጨት መስቀል ላይ ተሰቅሎ ያጣነውን ልጅነት አስገኘልን፤ ከጠፋንበት አግኝቶ ሕይወትን ሰጠ።

ተወዳጆች ሆይ !
ልብ ልንል የሚገባነው ነገር የሰው ልጆች የፈጠራቸውን ከመስቀል ወደኋላ እንዳላሉ ሁሉ የተሰቀበለበትን መስቀል እንኳ በምቀኝነት ተነሳስተው ከመቅበር አልተመለሱም፤ መስቀሉ ግን በኪሩቤል የሚቀመጠውን የተሸከመ፤ የእውነተኛው አዳኝ መሣሪያ እና የተዘጋው ሕይወታችን መዝገብ የተከፈተበት ነውና ተቀብሮ አልቀረም።
መስቀሉን በቆሻሻ ውስጥ የቀበሩት አይሁድ ባያውቁትም በክርስቲያኖች ልብ ውስጥ የመስቀሉን ቃል አብረው ነበር የቀበሩት፤ መስቀሉን ለጊዜው ያጠፉ ቢመስላቸውም ከአማኞች ልብ ውስጥ ግን ሊጠፋ አልቻለም፤ የጌታችን የማዳኑ ነገር እንዴት ከቶ ሊጠፋ ይችላል? የትኛውስ ኃይል ስለተደረገልን አምላካዊ ጥበብ የተሞላበት የማዳን ሥራ እንዳናስብ ያደርገናል? ይህንንስ ማድረግ ከቶ የሚቻል ነው? አይደለም !
መስቀል ሰላም የተሰበከበት፣ ድል የተቀዳጀንበትና ዲያብሎስን ድል የነሳንበት ምልክታችን ነው፤ ትናንትና ቅዱስ መስቀሉን የቀበሩ እና ሊያጠፉ የሞከሩ፤ የዛሬ ሰላም ጠልና የቤተ ክርስቲያን ጠላቶችን ይመስላሉ፤ ዛሬ በሀገራችን የሰላምና የፍቅር፣ የአንድነትና የወንድማማችነት መንፈስ እየጠፋ የጦርነት እና የእልቂት ድምጾች መሰማታቸውን እያስተዋልን እንገኛለን፣ ይህም ግልጽ የሆነ መስቀሉን (ሰላምን) የመቅበር ውጤት ነው፤ ዛሬ ፍቅርና ሰላም ከተሰበከበት የመስቀሉ ብርሃን ከተረጋገጠበት ጊዜ ወጥተን ወደጨለማና ወደኋላ እየሄድን የምንገኘው የሰላምን ጥቅም ስላልተረዳን አልያም ሆን ብለን ሰላምን ለማጥፋትና ሕይወታችንን በጦርነት ለመምራት በመዘጋጀታችን ነው፤ ይህም ጥፋትን የሚያስከትልና ከክርስቲያኖች የማይጠበቅ ተግባር ነው።
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት
ባለፉት ዓመታት በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በቆዩ ደም አፋሳሽ ጦርነቶች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የጥቃቱ ሰለባ የሆነችው ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ነች ያም ባይሆን ሀገራችንና ሕዝባችን በሚያሳዝን ሁኔታ የገፈቱ ቀማሽ ሆነዋል። በአሁኑ ወቅትም ሁሉም ለጦርነት የተሰለፉ ኃይሎች ጦርና የጦር ነገር ሀገርን ከማደኅየትና ሕዝብን ለተደራራቢ መከራ ከመዳረግ በቀር ይህ ነው የሚባል ጥቅም የሌለው መሆኑን በመገንዘብ መስቀሉን (ሰላምን) ከመቅበር ወጥተው እውነትንና ፍትሕን በማረጋገጥ ሕዝብን ለማገልገልና በእውነተኛነት ለመሥራት ቢተጉ የመስቀሉን አላማ ፈጽመው የሚከተሉ ይሆኑ ነበር።
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ "በመስቀሉ ገነትን ከፈተ፤ በመስቀሉ ድኅነትን አደረገ፤ አጋንንትን አባረረ፤ ከመስቀሉ ወርዶም ቤዛን አደረገልን።” ብሎ ቅዱስ ያሬድ እንደተናገረ እኛም መስቀሉን በማሰብ የሰላም ሐዋርያት፣ ጥልን የምናጠፋ፣ አንድነትንና ፍቅርን የምንሰብክ ልንሆን ይገባናል።
"በኃይለ መስቀሉ ይዕቀበነ ወይክሥት አዕይንተ አልባቢነ" እንኳን ለበዓለ ቅዱስ መስቀል በሰላምና በጤና አደረሰን አደረሳችሁ" መልካም በዓል !
አባ ሄኖክ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የደቡብና ምዕራብ አፍሪካ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ መስከረም ፲፮ ቀን ፳፻፲፱ ዓ.ም አዲስ አበባ፤ኢትዮጵያ

13 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.