Logo
ዳጉ-ጆርናል/Dagu-Journal
የዓለማችን የሙቀት መጠን በ3.25 ዲግሪ ሴልሺየስ ሊጨምር እንደሚችል አንድ ጥናት አመላከተ፡፡

​አስቸኳይ እና ከፍተኛ የካርቦን ልቀት ቅነሳ ካልተደረገ፣ የዓለማችን የሙቀት መጠን ቀደም ሲል ከተገመተው በላይ በ25 በመቶ ሊጨምር እንደሚችል ተመራማሪዎች አስታውቀዋል።

​በስዊዘርላንድ እና በጀርመን ተመራማሪዎች የተካሄደ አዲስ ጥናት እንደሚያመለክተው፣ አሁን ያሉ የፖሊሲ አቅጣጫዎች በተመሳሳይ ሁኔታ ከቀጠሉ እስከዚህኛው ክፍለ ዘመን ማጠቃለያ ድረስ የዓለማችን የሙቀት መጠን በ3.25 ዲግሪ ሴልሺየስ ሊያድግ ይችላል።

ይህም የስዊዘርላንድን እጅግ አስፊሪ የሚቲዮሮሎጂ ግምት ከእውነት የቀረበ ያደርገዋል። ​በኢ.ቲ.ኤች ዙሪክ እና በሌፕዚግ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች የተካሄደውን ይህን ጥናት ጠቅሶ ስዊስኢንፎ ማክሰኞ ዕለት እንደዘገበው፣ ቀደም ሲል የተደረጉ የካርበን ልቀት እና አየር ንብረት ግምቶች የወደፊቱን የሙቀት መጨመር አነስ አድርገው ገምተውት ሊሆን ይችላል።
 
የጥናቱ ዋና አዘጋጅ ገርጋና ጊዩሌቫ አስቸኳይ እና ከፍተኛ የልቀት ቅነሳ ካልተደረገ የሙቀት መጠኑን ቀደም ሲል ከተጠበቀው በ25 በመቶ ከፍ እንዲል ያደርገዋል ብለዋል። ​ይህ ግኝት በተለይም ከዓለም አቀፉ አማካይ በላይ ፈጣን የሙቀት መጨመር ለሚታይባት ለስዊዘርላንድ የጎላ አንድምታ አለው።

​​ባለፈው ህዳር ወር የተደረጉ ትንበያዎች እንደሚጠቁሙት፣ የ3 ዲግሪ ሴልሺየስ የሙቀት መጠን መጨመር በሚከሰትበት ወቅት በዙሪክ አካባቢ በመደበኛ የበጋ ወቅት የሙቀት መጠኑ ከ30 ዲግሪ ሴልሺየስ በላይ የሚሆንባቸው ቀናት ቁጥር 30 ገደማ ይደርሳል።
 
ተመራማሪዎቹ የትንበያ ስሌታቸውን ያሻሻሉት የተፈጥሮ የአየር ንብረት ልዩነቶችን እና በሳተላይት የተለኩ የመሬት የኃይል አለመመጣጠን መረጃዎችን፣ ማለትም ወደ መሬት የሚገባው የፀሐይ ኃይል እና ወደ ህዋ ተመልሶ የሚፈነጠቀው የሙቀት ልዩነትን ግምት ውስጥ በማስገባት ነው።ጥናቱ በተጨማሪም የሚፈቀደው ከፍተኛ የካርቦን መጠን ቀደም ሲል በነበሩ ሞዴሎች ከተገመተው በአንድ አምስተኛ ያህል አነስተኛ መሆኑን ጠቁሟል።
 
ሰላማዊ ነጋሲ
#ዳጉ_ጆርናል
18 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.