Logo
EBC
“ቅጠል ተራ” ወደ “መርካቶ የበጎነት መንደር” ተቀይሯል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
****************

የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የከተማ አስተዳደሩ በ“ቅጠል ተራ” በ4 ወራት ውስጥ የገነባቸውን 960 ቤቶች ዛሬ ለልማት ተነሺዎቹ መልሰው አስተላልፈዋል።

ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ባጋሩት መልዕክት፣ “ቅጠል ተራ”ን ለዜጎች ክብር ወደሚመጥን ንፁህ፣ አረንጓዴ የመኖሪያ ስፍራ መቀየር ያስቻለን ፈጣሪ ይመስገን ብለዋል።

የቀድሞው “ቅጠል ተራ” ለኑሮ እጅግ አስቸጋሪ፣ ለሰው ልጅ ክብር የማይመጥን፣ እጅግ የቆሸሸ፣ የተፋፈገ እና የተጨናነቀ በመሆኑ በእሳት አደጋ የነዋሪዎችን ሕይወት ጭምር አጥተናል ብለዋል።

ዛሬ ግን በስፍራው እጅግ ያማሩ፣ ዘመናዊና ሁሉም ነገር የተሟላላቸው 9 ባለ 9 ወለል ህንጻዎች ተገንብተው ሰፈሩ ወደ ምቹ የመኖሪያ አካባቢ ተቀይሯል ነው ያሉት።

ከንቲባ አዳነች በመልዕክታቸው እንዳሰፈሩት፣ "የመርካቶ የበጎነት መኖሪያ መንደር" በ11 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ በተገነቡ G+8 በሆኑ 9 ብሎኮች በአጠቃላይ 960 ቤቶችን ያካተተ ነው።

በውስጡም ሰፊ የስራ እድልን የሚፈጥሩ 371 የንግድ ሱቆች፣ የህጻናት የመጫወቻ ስፍራ፣ የስፖርት ማዘውተሪያ፣ ለነዋሪዎች የመኪና ማቆሚያ ፓርኪንግ፣ ለኤሌክትሪክ መኪና ቻርጅ ማድረጊያ፣ የውስጥ ለውስጥ አስፋልት መንገድ አለው።

ዘጠኙም ብሎኮች ላይ የጋራ መጠቀሚያ ሰገነት፣ ሊፍት፣ የፍሳሽና የኤሌክትሪክ መስመሮች ተሟልቶላቸው በዘመናዊ መልክ የተገነቡ ናቸው።

መርካቶ የበጎነት መኖሪያ መንደር በመርካቶ ዙሪያ “-ተራ” የሚል ቅጥያ ያላቸው (ቅጠል ተራ፣ ጭድ ተራ፣ ገብስ ተራ፣ ሳር ተራ፣ ቦንብ ተራ ወዘተ …) ጎስቋላ ሰፈሮችን ወደ ውብ የመኖሪያ አካባቢ የቀየረ የሰው ተኮር ልማት ጉልህ ማሳያ ነው።

ያለ እረፍት 24/7 በመሥራት፣ የተወሳሰበ ችግር ያለባቸው መሰል አካባቢዎችን የሰው ልጅ ክብርን ወደሚመጥኑ ምቹ የመኖሪያ መንደሮች ቀይረን አዲስ ሕይወት እንዲጀምሩ በማድረግ ቃል በተግባር መተርጎማችንን እንቀጥላለን ብለዋል ከንቲባ አዳነች።

ሥራዎቻችንን ሁሉ ሰው ተኮር በማድረግ አዲስ አበባን ውብ፣ ፅዱ፣ ለነዋሪዎቻችን የተመቸች ከተማ እንድትሆን ያለ እረፍት መሥራታችንን ይበልጥ አጠናክረን እንቀጥላለንም ብለዋል።

ካላቸው አካፍለው ከከተማ አስተዳደሩ ጎን በመቆም በበጎ ተግባር ላይ ለተሰማሩ፣ ዛሬም “ቅጠል ተራ” እንዲቀየር ላገዙ እና በግንባታው ለተሳተፉ ሁሉ ከንቲባ አዳነች በነዋሪዎች ስም ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል።

16 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.