Logo
YenetaTube
አሜሪካ ለሱዳኑ መሪ ጄነራል አብዱል ፋታህ አል ቡርሃን ቪዛ ከለከለች

አሜሪካ የሱዳን ወታደራዊ መሪ ጄነራል አብዱል ፋታህ አል ቡርሃን ወደ ግዛቷ ለመግባት ያቀረቡትን የቪዛ ጥያቄ ውድቅ ማድረጓ ተነገረ።

የፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው አሜሪካ የሱዳኑ መሪ በኒው ዮርክ እየተካሄደ ባለው በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ ነበር የአሜሪካን ቪዛ የጠየቁት።

አሜሪካ የቪዛ ክልከላውን በተመለከተ በይፋ የሰጠችው ማብራሪያ የሌለ ሲሆን፣ አንድ ምንጭ ለኤኤፍፒ እንደተናገሩት ቪዛውን የምትሰጠው "አል ቡርሃን ለሦስት ወራት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነትን ሲቀበሉ" እንደሆነ ገልጿል።

ነገር ግን ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጋር በደም አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ የሚገኘው በአል ቡርሃን የሚመራው የሱዳን ጦር ኃይል እንዲህ ዓይነቱ ፋታ ተቀናቃኙ መልሶ እንዲደራጅ እና ጥቃቱን እንዲቀጥል ዕድል ይሰጣል በሚል ተቃውሞታል።

የቪዛ ክልከላውን በተመለከተ የተመድ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤እርምጃው ድርጅቱን እንዳሳሰበው እና ዋና ፀሐፊው አሜሪካን እንደ አስተናጋጅ አገር ያለባትን ግዴታ በመፈጸም አል-ቡርሃን በአካል እንዲሳተፉ ቪዛውን እንድትሰጥ እያሳሰቡ መሆኑን ተናግረዋል።

አክለውም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጽህፈት ቤት ጉዳዩ እንደተሰማ ወዲያውኑ ከአሜሪካ ባለሥልጣናት ጋር መነጋገር እንደጀመረ እና ውይይቱም መቀጠሉን ገልጸዋል።

ጄነራል አል ቡርሃን የአገራት መሪዎች በሚሳተፉበት በዓመታዊው የመንግሥታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ በመገኘት ንግግር ለማድረግ ፕሮግራም ተይዞላቸው ነበር።

Ethio Fm

15 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.