Logo
FBC
ሰላም፣ እንደምን አደራችሁ?

የሰው ሰራሽ አስተውሎት፡ ለኢትየጵያ ሁለንተናዊ እድገት መፋጠን

በቀደሙት ጊዜያት ሀገራት የጦርነት አቅምን የሚያጎለብቱ መሳሪያዎችን መታጠቅ የኃይል ምንጫቸው አድርገው የሚቆጥሩት ራስን ማስከበሪያ መንገድ ነበር፡፡

ዛሬ ላይ ግን በኢኮኖሚና በፖለቲካ ዘርፉ ተፅዕኖ መፍጠሪያ እንዲሁም የፉክክር ዋነኛው መንገድ በቴክኖሎጂ የበላይነትን መያዝ ሆኗል፡፡

ዓለም በቴክኖሎጂ እየተራቀቀች በምትገኝበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ከዳር ተመልካችነት ወጥታ ወደ ዋና ተጋሪነት ለመቀላቀል የሚያስችል መንገድ ላይ እየተጓዘች ትገኛለች፤ ይህንንም በዘላቂነት ለማስቀጠልና የተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ በወጣቶች ላይ በተግባር እየተሰራ ነው፡፡

በዚህም የራስን አቅም በራስ ለመገንባትና የራስን ችግር በራስ ለመፍታት የሚያስችል ከአፍሪካ ፈር ቀዳጅ የሆነውን የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ገንብታ ወጣቶቿ ክህሎታቸውን የሚያዳብሩበትን መንገድ አመቻችታለች፡፡

ኢትዮጵያ በርካታ በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ያሏት እንደመሆኑ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ የአፈር ለምነትን፣ የአየር ንብረትና የተባይ በሽታዎችን ቀድሞ በመተንበይ ሀገሪቱ በምግብ ሉዓላዊነቷን ለማስከበር የምታደርገውን ጥረት የሚያግዝ ሆኗል፡፡

በሌላ በኩል በጤናው ዘርፍ የሕክምና ምስሎችን የሚተነትኑ፣ የጡት ካንሰር፣ ቲቢ፣ የሳንባ ሕመሞችን የሚለዩ ሶፍትዌሮች ተዘጋጅተዋል፡፡

የሰሌዳ ቁጥር ማሳወቂያ፣ የሰው ፊት ማሳወቂያ፣ በቪዲዮ የሚደረግ የትራፊክ ፍሰት መቆጣጠሪያ እንዲሁም ስማርት ፖሊስ ጣቢያዎች የመሳሰሉት ደህንነትን ከማስጠበቅ አንፃር ቴክኖሎጂውን ተከትለው የመጡ በረከቶች ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ የተለያዩ የተቋማት አገልግሎቶች እንዲሁም የትምህርት መርጃዎች የሚሰጡት በውስን ቋንቋዎች እንደመሆኑ ሀገሪቷ ያላትን 130 ሚሊየን በላይ ሕዝብ ያማከሉ ባለመሆናቸው በዚህ ቴክኖሎጂ አማካኝነት ተጨማሪ ቁጥር ያላቸው ቋንቋዎች ወደ መተግበሪያ እንዲጨመሩ በመሆኑ ለዜጎች ቋንቋዎችን ተርጉሞ የመረዳት እድል አሳድጓል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በብሪክስ መሪዎች ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር የሰው ሰራሽ አስተውሎት በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ለውጥን እውን ለማድረግ ወሳኝ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተዋል፡፡

በመሆኑም በዚህ ሰዓት ለኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ቅንጦት ሳይሆን ከልማትና እድገት አንፃር የሚቃኝ መሠረታዊ ከሚባሉት ነገሮች አንዱ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በሻንጋይ በተካሄደ ስብሰባ 29 ከሚሆኑ ሀገራት ጋር በመጣመር የዓለም አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ትብብር ድርጅት መስራች አባል በመሆን ተፈራርማለች፡፡ በቻይናና አሜሪካ ካሉ የቴክኖሎጂ ተቋማት ጋር የዳታ ሴንተር ግንባታና የክላውድ መሠረተ ልማት ስምምነቶችንም አድርጋለች፡፡

የዓለም ሀገራት ዛሬ ያሉበት ላይ ለመድረስ ብዙ ጊዜያትን ፈጅተዋል፤ ኢትዮጵያ ግን ያንን ረጅም መንገድ መጓዝ አይጠበቅባትም፤ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘመን ላይ በመሆናችን በቀላል መንገድ ለልማት እንድንፈጥን የሚያስችለን ጊዜ ላይ ነን፡፡

ስለሆነም ዘርፉን ይበልጥ ለማዘመን እና የሚሰጠውን ዘርፈ ብዙ ጥቅም ለማሳደግ የተጀመሩ ሥራዎችን በቁርጠኝነት ማጠናከር ይገባል፡፡

18 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.