Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር እና አንጋፋው የፖለቲካ ሰው ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና በቅርቡ የፌደራል መንግሥትን ለመታገል በማሰብ ስለተመሰረተው አዲስ ጥምረት ፓርቲያቸው እስካሁን የተለየ አቋም እንዳልያዘ አስታወቁ። ፕሮፌሰሩ ይህንን ያሉት በአዲሱ ጥምረት ዙሪያ ከዋዜማ ራድዮ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ ሲሆን፣ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተሉት መሆኑን ጠቅሰው ለጊዜው ዝርዝር አስተያየት ከመስጠት እንደሚቆጠቡ ገልጸዋል።

ይህ የፕሮፌሰር መራራ አስተያየት የተሰጠው ህወሓት፣ የኦሮሞ ነ*ፃነ*ት ሰ*ራዊት እና የአማራ ፋ*ኖ ኃይሎች "የህልውና ጥምረት" በሚል ስያሜ የጋራ ግምባር መፍጠራቸውን ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ፣ በአገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የጥምረቱን ዘላቂነት በተመለከተ ሰፊ የፖለቲካ ውይይት እየተካሄደ ባለበት ወቅት ነው።

የፖለቲካ ተንታኞች ለዘ-ሐበሻ እንደገለጹት ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና እና የኦፌኮ ወቅታዊ ዝምታ (ጊዜ የመግዛት ስልት) ከጀርባው ጥልቅ የፖለቲካ ስሌት አለው። በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል የሚያምነው ኦፌኮ፣ በአንድ በኩል በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ሰፊ የህዝብ መሰረት እና ወታደራዊ እንቅስቃሴ ካለው የኦሮሞ ነ*ፃነት ሰ*ራ*ዊት ጋር በተመሳሳይ የፖለቲካ ማህበረሰብ ውስጥ የሚንቀሳቀስ ነው። በዚህ እጅግ ፖላራይዝድ በሆነ የፖለቲካ ትኩሳት ውስጥ ኦፌኮ ይህንን አዲስ የትጥቅ ጥምረት በይፋ ቢደግፍ፣ ከመንግሥት በኩል የፓርቲውን ህልውና እስከመዝጋት እና አመራሮቹን እስከማሰር የሚደርስ ከባድ የህግ እርምጃ ሊያመጣበት ይችላል።

በሌላ በኩል ደግሞ ጥምረቱን ወጥቶ በጽኑ ቢያወግዝ፣ ከተቃዋሚው ጎራ ራሱን እንደማግለል ሊቆጠርበት ከመቻሉም በላይ፣ በተለይም ጥምረቱ ውስጥ ካለው የኦ*ነ*ሰ ደጋፊዎች እና ለዚያ ሀሳብ ዝንባሌ ካላቸው የራሱ የኦፌኮ አባላት ዘንድ ከፍተኛ የፖለቲካ ክስረትን ሊያመጣበት ይችላል። ስለዚህ ፕሮፌሰር መራራ "ገና አቋም አልያዝንም፤ አስተያየት አንሰጥም" ማለታቸው፣ ፓርቲያቸው ይህ አዲስ "የህልውና ጥምረት" በመግለጫ ደረጃ ይቀር ወይስ በተግባር የኃይል ሚዛን ይቀይራል የሚለውን የነገሮች መልክ እስኪጠራ ድረስ፣ ፖለቲካዊ ሚዛኑን ሳይስት የሚጠቀምበት ስትራቴጂካዊ ብልሃት መሆኑን ያመላክታል።

17 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.