Logo
FBC
የተዘረፉ ቅርሶችን በዲፕሎማሲያዊ ጥረት በማስመለስ ረገድ ውጤቶች ተመዝግበዋል - አሉላ ፓንክረስት (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የተዘረፉ ጥንታዊ ቅርሶችን በጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ወደ ሀገር በማስመለስ ረገድ ተጨባጭና አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል አሉ ተመራማሪና የኢትዮጵያ ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ አባል አሉላ ፓንክረስት (ዶ/ር)።

ባለፉት ሰባት ዓመታት የመደመር መንግሥት ኢትዮጵያ በጦርነት፣ በዝርፊያና በተለያዩ ምክንያቶች ያጣቻቸውን ጥንታዊ ቅርሶች በጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በማስመለስ ረገድ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ ተጨባጭና አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል።

አሉላ ፓንክረስት (ዶ/ር) እንደሚሉት ፥ ኢትዮጵያ በተለያየ አጋጣሚ ሕገወጥ በሆነ መልኩ የወጡ ቅርሶችን ለማስመለስ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተቀናጀ መልኩ እየሰራች ነው።

በኃይልና በዘረፋ የተወሰዱ ቅርሶች ሁልጊዜም ወደ መጡበት የታሪክ ባለቤት መመለስ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ቅርሶች በተለያዩ የውጭ ሀገራት ገበያዎችና ለጨረታ ሽያጭ በሚቀርቡበት ወቅት፣ ሕጋዊና ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ተቃውሞዎችን በማቅረብ ጨረታዎቹ ሙሉ በሙሉ እንዲሰረዙ ማድረግ ተችሏልም ብለዋል።

ጨረታዎቹ ከተሰረዙ በኋላም መንግሥትና ባለድርሻ አካላት በመደራደር በርካታ ታሪካዊ ቅርሶችን መታደግ መቻሉንም አንስተው በአሁኑ ወቅትም ከመቅደላ ተዘርፎ ለሽያጭ የቀረበውን የዓጼ ቴዎድሮስ ወንጌል ለማስመለስ መንግሥት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ከዓለም አቀፍ ሙዚየሞች ጋር በቀጥታ በመደራደር ቅርሶችን ማስመለስ ሌላው ውጤታማ ስልት ሆኖ በመተግበር ላይ እንደሆነ እና ‎በዚህም ከአሜሪካው ቶሌዶ ሙዚየም ብቻ ወደ 380 ገደማ የኢትዮጵያ ቅርሶች ደረጃ በደረጃ ለመመለስ ስምምነት ላይ መደረሱን አመልክተዋል።

በቅርቡ ሁለት የ15ኛው ክፍለ ዘመን ብራናዎችን እና ሦስት መስቀሎችን እንደሚመልስ እንዲሁም ቀሪዎቹን ቅርሶች በሚቀጥሉት ከ5 እስከ 10 ዓመታት ውስጥ በሂደት ለመመለስ ፈቃደኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ባለፉት ዓመታት ቅርሶችን በማስመለስ በኩል በመንግስት በኩል የታየው ቁርጠኛ የዲፕሎማሲ ብቃት የሚደነቅ ነው ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

19 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.