Logo
FBC
ቀይ ባሕር፡ ለኢትዮጵያ የሚሰጠው ስትራቴጂካዊ ትርጉም

አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ቀይ ባሕር የዓለም ንግድና ደህንነት ዋና መስመር ሲሆን ለኢትዮጵያ ደግሞ የኢኮኖሚና የስትራቴጂ ዋና ጥያቄ ነው።

ቀይ ባሕር ዛሬ የንግድ መስመር ብቻ አይደለም። የዓለም ንግድ፣ የኃይል አቅርቦትና የቀጣናዊ ደህንነት የሚገናኙበት ወሳኝ የጂኦፖለቲካ ማዕከል ሆኗል።

በተለይም የባብ አል መንደብ ባሕረ ሰላጤ ለዓለም የባሕር ንግድ ያለው ሚና የክልሉን ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ የበለጠ አጉልቶታል።

ኢትዮጵያ የባሕር ዳርቻ የሌላት ሀገር ከሆነች በኋላ የውጭ ንግዷ በአጎራባች ሀገራት ወደቦችና በሚያገናኙት የመጓጓዣ መስመሮች ላይ ተመስርቷል። ይህ ሁኔታ የወደብ አገልግሎት፣ የመጓጓዣ ወጪና የንግድ ቀጣይነትን ከውጫዊ ሁኔታዎች ጋር ያገናኛል።

በመሆኑም የተረጋጋና ተገማች የባሕር መዳረሻ ማግኘት ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ጥቅም ብቻ ሳይሆን የረጅም ጊዜ ስትራቴጂካዊ ጉዳይ ነው።

በዚህም ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድና በጋራ ጥቅም ላይ ተመስርታ መብቷን ለማረጋገጥ የሚቻላትን ሁሉ በማድረግ ላይ ትገኛለች።

በሌላ በኩል በቀይ ባሕርና በባብ አል መንደብ አካባቢ የሚታዩ የደህንነት ስጋቶች የዓለም የባሕር ንግድ ላይ ተጽዕኖ ማሳደራቸውን ቀጥለዋል። ይህም መርከቦች ረዘም ያለ መንገድ እንዲጓዙ ሲገደዱ የጊዜና የመጓጓዣ ወጪ ይጨምራል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ቀይ ባሕር በዓለም ላይ እጅግ ስትራቴጄካዊ እና ለደህንነት ስጋት ተጋላጭ ከሆኑ የባሕር መስመሮች አንዱ እየሆነ መጥቷል። ቀይ ባሕርን ከኤደን ባሕረ ሰላጤ የሚያገናኘው የባብ አል መንደብ ባሕረ ሰላጤም ለጥቃትና ለመጓጓዣ መስተጓጎል ተጋላጭ ሆኖ ቀጥሏል።

ይህም አንዳንድ የዓለም የመርከብ ኩባንያዎች በአፍሪካ ደቡባዊ ጫፍ በኩል ረዘም ያለ መንገድ እንዲጠቀሙ በማድረግ የመጓጓዣ ወጪን እያሳደገ ነው።

ይህም ለኢትዮጵያ የባሕር መዳረሻ የንግድ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሀገር የረጅም ጊዜ ስትራቴጂካዊ አማራጭ መሆኑን ያሳያል፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄን ጉዳይ አደባባይ ይዛ ስትወጣ ታዲያ ለቅንጦት ሳይሆን ከላይ የተዘረዘሩት የደህንነት ጉዳዮችን ጨምሮ ሌሎችም ስትራቴጅኪያዊ ጠቀሜታዎችን ለማግኘት ነው፡፡

በአቤል ነዋይ

22 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.