Logo
Getu Temesgen
የኢትዮጵያን አትክልትና ፍራፍሬ ልማት በታዳሽ ኃይል የሚያበለጽገው አዲሱ ፕሮግራም ተበሰረ
#ethiopia | ​በኢትዮጵያ የአትክልትና ፍራፍሬ (ሆርቲካልቸር) ሴክተርን በዘላቂነት እና በአየር ንብረት ለውጥ በሚቋቋም መንገድ ለማሳደግ ያለመው "ሆርቲ-ላይፍ ግሪን ግሮውዝ" የተሰኘ አዲስ ፕሮግራም በአዲስ አበባ በይፋ ተጀመረ።

ዓለም አቀፉ የልማት ድርጅት ኤስ.ኤን.ቪ (SNV) ከአውሮፓ ህብረት እና ከኔዘርላንድስ ኤምባሲ በተገኘ የፋይናንስ ድጋፍ ይፋ ያደረገው ይህ ፕሮግራም በአገሪቱ በሚገኙ ሰባት ክልሎች ውስጥ የሚተገበር ሲሆን የአነስተኛ አርሶ አደሮችን ሕይወት ለመለወጥ ትልቅ ተስፋ ጥሏል።

​ከፈረንሳይኞቹ 2016 ጀምሮ ሲተገበር የቆየውን የሆርቲ-ላይፍ ስኬቶች መሠረት በማድረግ የተነደፈው ይህ አዲስ ምዕራፍ በተለይም ታዳሽ ኃይልን ለግብርና ምርታማነት የማዋል (PURE) ስልት ላይ ትኩረት አድርጎ ይሠራል።

በዚህም አርሶ አደሮች በፀሐይ ኃይል የሚሠሩ የመስኖ ሥርዓቶችን፣ የፀሐይ ኃይል ማቀዝቀዣዎችን፣ የማድረቂያ ቴክኖሎጂዎችን እና የባዮዳይጀስተር አጠቃቀምን እንዲያስፋፉ ይደረጋል።

እነዚህ ዘመናዊ አቀራረቦች ምርታማነትን ከመጨመር ባለፈ ከምርት ስብሰባ በኋላ የሚባክነውን የሰብል መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀንሱ እና የውኃ አጠቃቀምን ውጤታማ እንደሚያደርጉ ተገልጻል።

​በይፋዊ የማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደተገለጸው የአትክልትና ፍራፍሬ ክፍለ-ኢኮኖሚ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ወሳኝ ሚና ይጫወታል።

የኤስ.ኤን.ቪ ተወካዮች እንደገለጹት፣ አዲሱ ፕሮግራም ከአርሶ አደሮች፣ ከግል ባለሀብቶች፣ ከፋይናንስ ተቋማት እና ከመንግሥት አካላት ጋር በቅንጅት በመሥራት አዳዲስ የገበያ ትስስሮችን ይፈጥራል። ይህ ቅንጅታዊ አቀራረብ አርሶ አደሮች የቴክኖሎጂና የፋይናንስ አገልግሎቶችን በቀላሉ እንዲያገኙ ከማስቻሉም በላይ የአካባቢ ጥበቃን እና ዘላቂ የግብርና ልማትን ያረጋግጣል።

​በመጨረሻም ፕሮግራሙ በሰብሎች ጥራትና መጠን ላይ የሚታይ ለውጥ በማምጣት የአነስተኛ አርሶ አደሮችን ገቢ ያሳድጋል ተብሎ ይጠበቃል።

ተፈጥሮአዊ ሀብቶችን በአግባቡ በመጠቀም እና የታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂዎችን በማስፋፋት ኢትዮጵያ የጀመረችውን የግብርና ትራንስፎርሜሽን እና የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም አቅም ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ፕሮግራሙ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ታምኖበታል።

በተጨማሪም በግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር አማካሪው በፕ/ር አሊ የተመራ የባለድርሻ አካላት ፓናል ውይይት ተካሂዷል።

📸 ከበደ መክብብ

በያፌት ገ/ህይወት

Getu Temesgen - (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu

24 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.