Logo
Getu Temesgen
ጀፎረ
#ethiopia | ጉራጌዎችን ታታሪ ጥበበኛ ከሚያሰኟቸው ነገሮች ውስጥ የመንደር አቀያየሳቸውና የሳር ቤት አሠራራቸው ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በተለይ ደግሞ ማራኪ የመንደር ገጽታ እንዲኖራቸው ከጥንት ጊዜ ጀምረው የሚታወቁበት የምሕንድስና ጥበብ አስደማሚ ነው፤ ‹ጀፎረ›› ይባላል፡፡

በጉራጊኛ ‹ጀፎረ›› ማለት አውራ መንገድ ማለት ነው፡፡

‹ጀፎረ›› ከመሠረታዊ ጠቀሜታው ባለፈ ለጉራጌ መንደሮች ውበትን በማላበስ የጎላ አስተዋጽኦ አለው፡፡

በጉራጌ የመንደር አመሠራረት ያለ ጀፎረ አይታሰብም፡፡

ጀፎረ አረንጓዴ ሳር የለበሰ እና በሁለት ትይዩ መንደርተኞች መካከል የሚገኝ ሰፊና ማራኪ አውራ መንገድ ነው፡፡

ለአካባቢው ነዋሪዎች መግቢያና መውጫ እንዲሁም መተላለፊያ ሆኖ ያገለግላል፡፡
እስከ 60 ሜትር ድረስ ስፋት ያለው ይኽ የወል መንገድ ከመንገድነት ባሻገር ለተለያዩ ማኅበራዊ ኩነቶች ያገለግላል፡፡

‹ጀፎረ›› ለማኅበረሰቡ እንደሠርግ ያሉ የደስታ፣ እንደለቅሶ ያሉ የሐዘን ማኅበራዊ ሥነ ሥርዓቶች መከወኛ ስፍራም ነው፡፡

በሠርግ ወቅት ሰርገኞች የሚጨፍሩበት፣ አባቶችና እናቶች እንዲሁም የሰፈር አዛውንቶች ልጆቻቸውን መርቀው የሚሰጡበት ቦታ ነው፤ ‹ጀፎረ››፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ‹ጀፎረ›› የተለያዩ ስብሰባዎች፣ እንደ ፈረስ ጉግስና መሰል ባህላዊ ትዕይንቶች የሚካሄዱበትም ነው፡፡

የጉራጌ እረኞች ከብቶቻቸውን የሚያመላልሱበት በዚሁ ‹ጀፎረ›› በተባለው የወል ስፍራ ነው፡፡

በጉራጌ ባህል ‹ጀፎረ›› ወይም ባህላዊ አውራ መንገድን አጥሮ ወደ ግል ማካለል የተወገዘ ተግባር፤ ነውርም ነው።

ይህን ስርዓት ተላላልፎ የተገኘ ግለሰብ ቢኖር በማኅበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያጣል፤ ከማንኛውም ማኅበራዊ ግንኙነት ይገለላል፡፡
በጉራጌዎች ዘንድ በየዓመቱ በድምቀት የሚከበረው የዓረፋና የመስቀል በዓል በዚህ የወል ስፍራ ላይ ነው የሚከወነው፡፡

በበዓሉ ልጃገረዶችና ጎረምሶች ከሥነ ሥርዓቱ በኋላ ባህላዊ ጨዋታዎችን የሚጫወቱበት ስፍራም ነው፤ ‹ጀፎረ››፡፡

‹ጀፎረ›› በአሁን ወቅት የሃገሪቷን ማህበረሰብ ቀልብ ስቦ የከተማና የገጠር ኮሪደር ምሳሌ ሆኗል።

የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች ‹ጀፎረ››ን ለመጎብኘት ወደ ጉራጌዎች ምድር ማቅናታቸው በህዝቡ ዘንድ ደስታን ፈጥሯል።

OBN

1 year ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.