Logo
EBC
ኢትዮጵያ በማዕድን፣ በታዳሽ ኢነርጂና በኢንዱስትሪ ጠንካራ አጋርነት ለመገንባት ዝግጁ ናት - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
******************

ኢትዮጵያ በማዕድን፣ በታዳሽ ኢነርጂ እና በኢንዱስትሪ ዘርፍ ጠንካራ አጋርነት ለመገንባት ዝግጁ መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡

18ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ ዛሬ በህንድ ኒው ዴልሂ መካሄድ ጀምሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያን እና የአፍሪካን አህጉራዊ አቋም በግልፅ አስቀምጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው፤ ሀገራት በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ያላቸው ውክልና ፍትሃዊ መሆን እንዳለበት ገልጸው፤ ውክልናው ተጨባጭ ውጤት ማምጣት እንዳለበትም አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ መሰረታዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን በማካሄድ እና የውጭ ኢንቨስትመንቷን እንደገና በማዋቀር ላይ ከሚገኘው የቅርብ ጊዜ ልምዷ በመነሳት ጫና ውስጥ ላለ ማንኛውም ኢኮኖሚ ጊዜ ትልቅ ዋጋ የሚያስከፍል በመሆኑ የብድር መፍትሔዎች ፈጣን ግልጽ እና አስቀድመው የሚገመቱ ሊሆኑ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

እንደ ኢነርጂ ሽግግር፣ ዘመናዊ ማኑፋክቸሪንግ እና የዲጂታል ኢኮኖሚ ያሉ የወደፊት የልማት መስኮች ሙሉ በሙሉ በማዕድናት ላይ የተመሰረቱ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንስተዋል፡፡

አፍሪካ የነዚህ በርካታ ሀብቶች ባለቤት እንደመሆኗ መጠን በብሪክስ አባል ሀገራት ዘንድ የሚገኘውን ካፒታል ቴክኖሎጂ እና ሰፊ የገበያ ዕድል በማጣመር ሀብቶቹ በሚገኙበት ስፍራ የተሻለ ተጨማሪ እሴት መፍጠር እንደሚገባ አሳስበዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ በማዕድን፣ በታዳሽ ኢነርጂ እና እየጎለበተ በሚገኘው የኢንዱስትሪ መሰረቷ ዙሪያ ጠንካራ አጋርነቶችን ለመገንባት ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለአህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ትስስር ያላት አበርክቶ ከፍተኛ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን ከዓለም ጋር እያገናኘ እንደሚገኝ በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት የምታቀርበው የኤሌክትሪክ ኃይል ለሀገራቱ ኢኮኖሚ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በብሪክስ እና በአፍሪካ ህብረት መካከል የሚደረገው ግንኙነት ከአጀንዳ 2063 ጋር በተሻለ ሁኔታ እንዲጣጣም ጠንካራ የምክክር መድረክ እንዲኖር ኢትዮጵያ የምትደግፍ መሆኑን አመልክተዋል።

በብሌን ደምበሎ

27 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.