Logo
EBC
የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ሉዓላዊነት እና የትውልድ ተሻጋሪ ብልጽግና መንገድ፡ የአዲሱ ዓመት አቅጣጫ
*****************

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አዲሱ ዓመት ሁለንተናዊ ሉዓላዊነታችን ይበልጥ የሚከበርበት፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን ይበልጥ የሚጸናበት፣ በሁሉም ዘርፎች የጀመርነው ምርታማነት በዓይነትና በጥራት የሚጨምርበት፣ ሀገራችንም የቀጣናው እና የአፍሪካ መሪነቷን ሥር መሠረት የምታስይዝበት እንዲሁም የኢትዮጵያ ብልጽግና ትውልድ ተሻጋሪ እንዲሆን ተደርጎ የሚገነባበት ዓመት እንደሚሆን አመላክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአዲሱ ዓመት ያስተላለፉት ይህ መልዕክት፣ የነባር ስኬቶችን ቀጣይነት የሚያረጋግጥና የሀገራችን መፃኢ እድል ግልጽ በሆነ ስትራቴጂካዊ እይታ የሚያመላክት እንዲሁም የሀገራችንን ዘመናዊ የልማትና የፖሊሲ አቅጣጫዎች በግልጽ የሚያንጸባርቁ ናቸው።

ሀገራዊ ሉዓላዊነት ከባህላዊው የድንበር ጥበቃ አስተሳሰብ ተሻግሮ የምግብ፣ የዲጂታል፣ የኢኮኖሚ እና የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነትን የሚያካትት እንደሆነ ተስፋ ተጥሎበታል።

በምግብ ራስን የመቻል ጥረት፣ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እና በቴክኖሎጂ እድገት የሚመዘገቡ ስኬቶች ሀገራችን በውጫዊ ጫናዎች ሳትበገር በራሷ እግር እንድትቆም የሚያስችሉ የሁለንተናዊ ሉዓላዊነት መሠረቶች ናቸው።

የኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማት መሠረት የኅብረ ብሔራዊ አንድነቷ ጥንካሬ ነው። አዲሱ ዓመት የሕዝቦችን አብሮነት በሚያጠናክሩ፣ በውይይትና በምክክር ሂደቶች እንዲሁም የጋራ እሴቶችን በሚያጎሉ ተግባራት የታጀበ እንደሚሆን ይጠበቃል። ልዩነቶችን በውይይት በመፍታትና የጋራ ማንነትን በመገንባት ሂደት ሀገራዊ አንድነት ይበልጥ እንደሚጸና ያመላክታል።

ባለፉት ዓመታት በግብርና እንደ “ሌማት ትሩፋት” ያሉ ፕሮግራሞች፣ በኢንዱስትሪ “ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ እና በአገልግሎት ዘርፎች የተጀመሩት ሥራዎች አሁን ወደ አዲስ ደረጃ የሚሸጋገሩበት ምዕራፍ ላይ ይገኛሉ። ትኩረቱም ከምርት መጠን መጨመር ባሻገር የምርቶችን ዓይነት ማስፋፋትና የጥራት ደረጃቸውን በማሳደግ በሀገር ውስጥና በውጭ ገበያ ተወዳዳሪ ማድረግ ላይ ይሆናል።

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካና በመላው አህጉሪቱ የምትጫወተው ዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊና መሰረተ-ልማታዊ ሚና ይበልጥ የሚጎላበት ዓመት ይሆናል። የኃይል አቅርቦት ትስስር፣ የቀጣናዊ የንግድ ማቀላጠፍ፣ የአቪዬሽንና የሎጂስቲክስ ኤክስፓንሽን እንዲሁም የአካባቢ ጥበቃ እንቅስቃሴዎች ሀገራችን በቀጣናውና በአፍሪካ ያላትን መሪነት በጽኑ መሠረት ላይ የሚያስቀምጡ ናቸው።

ልማት ለዛሬው ትውልድ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን፣ ለነገው ትውልድ የተሻለች ሀገር የሚያስረክብ መሆን አለበት። እንደ ኮሪደር ልማት ያሉ የከተሞች ዘመናዊነት፣ የሜጋ ፕሮጀክቶች ግንባታ፣ የአካባቢ ጥበቃ እና በሰው ሀብት ልማት እንደ የኮዲንግና ዲጂታል ክህሎት ስልጠናዎች ላይ የሚደረጉ ኢንቨስትመንቶች ሁሉ ትውልድ ተሻጋሪ የሆነ ጠንካራ የብልጽግና መሠረት የሚጥሉ ናቸው።

በመሆኑም የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት ግልጽ የሆነ ሀገራዊ ራዕይን የሚያስቀምጥ ሲሆን፣ የተጣሉትን ግቦች ለማሳካት የሁሉም ዜጋ የተቀናጀ ጥረት፣ የሥራ ባህል ማደግና ለጋራ ዓላማ መቆም ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ።

በአድማሱ አራጋው
#ethiopia #ebc #pmabiyahmed #sovereignty #ethiopianprosperity

27 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.