Logo
Getu Temesgen
የቅቤ እቁብ (ዊጂኦ)
ከያሆዴ ድምቀት ጀርባ ያለው ጥበብ
#ethiopia | በወርኃ መስከረም የሀዲያ ምድር በአደይ አበባ ትሸለማለች፤ የክረምቱ ዝናብ ያደፈረሳቸው ምንጮችና ጅረቶች ይጠራሉ። ከከላላሞ ጫፍ እስከ ሾንቆላ ተራራ፣ ከመጨፈራ ዳርቻ እስከ ቦዮ ሐይቅ ወሽመጥ ድረስ ተፈጥሮ ለታላቁ የያሆዴ በዓል ትዘጋጃለች።

ከመስከረም እስከ ህዳር የሀዲያ አውድማዎች በሳቅና በእልልታ ይሞላሉ። የዓመቱ ድካም በደስታ የሚረሳበት፣ የበረከት ወቅት ነው።

ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ድግስና ፈንጠዝያ እንዴት ያለ ኢኮኖሚያዊ ጫና ይከናወናል?

መልሱ “ዊጂኦ” — የቅቤ እቁብ በሚባለው ባህላዊ የቁጠባ ሥርዓት ውስጥ ይገኛል።

የሀዲያ ተወላጅ የሆኑት ወ/ሮ እንዳሻሽ ፀጋዬ ለኢቢሲ ሳይበር እንዳስረዱት፣ የያሆዴ በዓል በአጋጣሚ የሚከወን ድግስ ሳይሆን፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፈ የቁጠባና የዕቅድ ባህል ውጤት ነው።

የቅቤ እቁብ — ዊጂኦ

የያሆዴ በዓል እንዳበቃ እናቶች ከ4 እስከ 6 ሆነው የቅቤ እቁባቸውን ይጀምራሉ። የሚሰበሰበው ጥሬ ቅቤ በአንዷ እናት ቤት በማሰሮ ውስጥ በጥንቃቄ ይቀመጣል።

ከስድስት ወር በኋላ የበሰለው ቅቤ ይሸጣል፤ በቦታውም አዲስ ቅቤ ይተካል። በዚህ መልኩ የቁጠባው ሰንሰለት ሳይቋረጥ ይቀጥላል።

የእንሰት ቁጠባ — “ሄንቼሳ”

ከቅቤ እቁብ ጎን ለጎን የእንሰት ቁጠባም ይካሄዳል። በደቦ የሚፋቀውና በየጊዜው እየተጨመረ የሚዘጋጀው ቆጮ “ሄንቼሳ” ወይም የዓመት ቆጮ ይባላል።

ነሐሴ ሲገባ እናቶች በዓመቱ ያከማቹትን የቅቤና የቆጮ ድርሻ በፍትሃዊነት ይከፋፈላሉ። መስከረም ሲጠባ ቤታቸው በምግብና በበረከት ሞልቶ እንግዳን ለመቀበል ይዘጋጃሉ።

ዊጂኦ የቁጠባ ሥርዓት ብቻ አይደለም።

ይህ ባህላዊ ሥርዓት የመተማመን፣ የመተሳሰብ፣ የመተጋገዝና አብሮ የመኖር ፍልስፍናን የሚያሳይ የሀዲያ ሕዝብ የኢኮኖሚ ጥበብ ነው።

በዘመናዊ የፋይናንስ ተቋማት በፊት የነበረ ይህ የቁጠባ ባህል፣ በጋራ ጥረት የዓመቱን ድካም ወደ በረከት የመቀየር ጥበብን ያስተምራል።

ዊጂኦ — የገንዘብ ቁጠባ ብቻ ሳይሆን፣ የአንድነት፣ የመከባበርና የአብሮነት መገለጫ!

ከሀዲያ እናቶች ጥበብ እንማር፤ በመተሳሰብና በመተጋገዝ የተሻለ ነገን እንገንባ።

መልካም አዲስ ዓመት!

ናኒ ከሆሳዕና

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.