Logo
FastMereja
አፍሪካ የ-Al ቴክኖሎጂ ተቀባይ ብቻ ሳትሆን ፈጣሪ የምትሆንበትን መሠረት የጣለው አውደ ጥናት ተካሄደ!
#fastmereja :- "ለአፍሪካ ማህበረሰብ ተግዳሮቶች መፍትሔ የሚሰጡ መሠረታዊ ሞዴሎች" በሚል መሪ ቃል ለአራት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የACT-Africa 2026 አውደ ጥናት በአዲስ አበባ ሃያት ሬጀንሲ ሆቴል በዛሬዉ እለት ተጠናቋል።

በአፍሪካ እና በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ተመራማሪዎችን፣ የመረጃ ሳይንቲስቶችን እና ፖሊሲ አውጪዎችን ያሰባሰበው ይህ መድረክ፤ የአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ (AI) ቴክኖሎጂዎችን ከአፍሪካ ልዩ ሁኔታዎች፣ ቋንቋዎች እና የልማት ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ዘርፎች ጋር ማጣጣም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ትኩረት በማድረግ ነዉ የተካሄደዉ።

ዝግጅቱ በሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ የመረጃ እና አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ማህበረሰብ ተቋም (MIDAS) ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር እና በሽሚት ሳይንሶች የገንዘብ ድጋፍ የተዘጋጀ ሲሆን፣ ዓላማውም አፍሪካውያን ባለሙያዎች የውጭ ሞዴሎችን በቃል ከመቀበል ይልቅ የራሳቸውን መፍትሄዎች እንዲገነቡ ማብቃት መሆኑ ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ እና ግንባታ አካባቢ ኮሌጅ ተመራማሪዎችና የACT-Africa 2026 ዋና አስተባባሪዎች ዶ/ር ዮናስ ምናሉ እማኙ እና ዶ/ር ደሳለኝ ወገሶ እንደገለጹት፤ መድረኩ በአህጉሪቱ ስነ-ምህዳር ውስጥ ለሚሰሩ ተመራማሪዎች የእውቀት ልውውጥና ጠንካራ አጋርነት ለመፍጠር ያለመ ስለመሆኑ ነዉ የገለፁት።

በአዘጋጅነት ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ከኡጋንዳ እና ኬንያ የመጡ ከፍተኛ ተመራማሪዎች የተሳተፉበት ይህ አውደ ጥናት፣ ተሳታፊዎች ከመሠረታዊ ንድፈ-ሐሳብ እስከ ተግባራዊ አተገባበር ያተኮሩ ስልጠናዎችን እንዲወስዱ ያስቻለ ሲሆን በተለይም በግብርና፣ ጤና፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ መሠረተ ልማት እና የአየር ንብረት ለውጥ ዘርፎች ላይ ያተኮረ የሀካቶን ውድድር ተካሂዶ ተግባራዊ መፍትሄዎች ቀርበዋል።

ከስልጠናው ባሻገር ተሳታፊዎች የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ኢንስቲትዩትን የጎበኙ ሲሆን፣ ዝግጅቱ ከመጪው የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት በዓል ጋር ተገጣጥሞ በመካሄዱ እንግዶች የሀገሪቱን ባህል እንዲለማመዱ እድል ፈጥሯል።

በአጠቃላይ አውደ ጥናቱ አፍሪካ በዓለም አቀፍ የአርቲፊሻል ኢንተሊጂየንስ (AI) ሥርዓተ-ምህዳር ውስጥ የቴክኖሎጂ ተቀባይ ብቻ ሳትሆን የራሷን ፈጠራ የምታመነጭበትን መሠረት በመጣል ተጠናቋል።

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.