Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) በከተሞች እያሻቀበ የመጣው የኑሮ ውድነት በነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ ይገኛል። የዋጋ ንረቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመሩ፣ በተለይም ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል በእጅጉ እየጎዳው ነው።

ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የእንጅባራ ከተማ ነዋሪ የሆኑትና በመንግሥት ሥራ የሚተዳደሩት አቶ ቢተው መለሰ፣ የገበያው ዋጋ ባልተጠበቀ ሁኔታ መጨመሩን በሀዘኔታ ይገልጻሉ። አቶ ቢተው እንዳሉት፣ ከዚህ ቀደም ከ350 እስከ 500 ብር ይገዛ የነበረው አምስት ሊትር የምግብ ዘይት ዛሬ ከ2,000 ብር በላይ ሆኗል፤ ከ30 እስከ 50 ብር ይሸጥ የነበረው ቀይ ሽንኩርት ከ130 እስከ 140 ብር ደርሷል፤ የድሀው የዕለት ጉርስ የሆነው በቆሎ እንኳን ከ3,500 ብር ወደ 7,500 ብር አሻቅቧል።

የኑሮ ጫናው በምግብ ሸቀጦች ላይ ብቻ ሳያበቃ የትራንስፖርት፣ የቤት ኪራይ፣ የውኃ ክፍያ እና የልጆች ትምህርት ቤት ወጪ ተዳምሮ የሠራተኛውን ጫንቃ አጎብጦታል። አራት ልጆች ያሏቸው አቶ ቢተው፣ የኑሮን ጫና ለመቋቋም ሦስት ልጆቻቸውን ከግል ትምህርት ቤት አስወጥተው በመንግሥት ትምህርት ቤት እንዲማሩ ለማድረግ ተገደዋል። "መንግሥት የሠራተኛውን ደመወዝ በትንሹ ሲጨምር፣ ነጋዴው ያንኑ ሰበብ አድርጎ በእጥፍ ድርብ ዋጋ ይጨምራል፤ በዚህም የተሻለ ደመወዝ አለኝ የሚለው ሠራተኛም ኑሮን መግፋት አቅቶታል" በማለት ቅሬታቸውን አቅርበዋል።

የኑሮ ውድነት ዜጎችን ክፉኛ በሚፈትንበት በዚህ ወቅት፣ ገበያን ለማረጋጋት እና የሸማቹን እንባ ለማበስ የኅብረት ሥራ ማህበራት ግንባር ቀደም ሚና አላቸው። ትርፍን ብቻ ከሚያሳድደው የንግድ አሠራር ወጣ ብለው፣ ማህበራቱ ምርትን በቀጥታ ከአምራች ወደ ሸማች በማድረስ ፍትሐዊ የዋጋ ሥርዓት እንዲኖር ይሠራሉ።

የዳንግላ ከተማ አሥተዳደር የኅብረት ሥራ ማህበራት ማስፋፊያ ቡድን መሪ ወ/ሮ አልማዝ ጌታነህ እንዳሉት፣ በከተማዋ "የጡረተኞች" እና "የአንድነት ሸማቾች" የተሰኙ ማህበራት ይገኛሉ። እነዚህ ማህበራት የግብርና ምርቶችን ከአርሶ አደር የኅብረት ሥራ ማህበራት፣ የኢንዱስትሪ ምርቶችን ደግሞ (እንደ ዘይት እና ስኳር) ከአድማስ ዩኒየን፣ ከቡሬ ኢንዱስትሪ እና ከጅንአድ በቀጥታ በማስመጣት በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረቡ ነው። ይሁን እንጂ ማህበራቱ ያላቸው የካፒታል አቅም አነስተኛ መሆን የሸማቹን ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ለማሟላት እንቅፋት ሆኖባቸዋል። ማህበራቱን ለመደገፍ 7 ሚሊዮን ብር የተጠየቀ ቢሆንም፣ ሊፈቀድ የቻለው 2 ሚሊዮን ብር ብቻ መሆኑን አስታውሰው፣ ሕዝቡ የማህበራቱ አባል በመሆን አቅማቸውን እንዲያሳድግ ጥሪ አቅርበዋል።

የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ኅብረት ሥራ ማህበራት ማስፋፊያ ተጠሪ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብርሐም ዳኛው በበኩላቸው፣ የማኅበራቱ ዓላማ የምርት አቅርቦት ሰንሰለትን በማሳጠር እና የደላሎችን ጣልቃ ገብነት በማስቀረት ገበያን ማረጋጋት መሆኑን አብራርተዋል። በዋጋ፣ በጥራት እና በተደራሽነት ከግል ነጋዴው የተሻለ አገልግሎት እንደሚሰጡም ጠቅሰዋል። ለበዓላት ገበያን ለማረጋጋት ከ18 ሺህ እስከ 20 ሺህ ኩንታል የግብርና ምርት፣ እንዲሁም ከ18 ሺህ ኩንታል በላይ የኢንዱስትሪ ምርት ለማቅረብ እየተሠራ መሆኑንና ለዚህም መንግሥት ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ ተዘዋዋሪ ብድር መመደቡን አስታውቀዋል።

በክልል ደረጃ የተሰሩ ሥራዎች እና ሕገ-ወጥነትን የመቆጣጠር እርምጃ
የገበያ ዋጋ መናር የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የክልሉ እና የሀገሪቱ ችግር ነው። የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ማህበራት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ጌትነት አማረ እንዳሉት፣ በአጠቃላይ ከ560 ሺህ ኩንታል በላይ የግብርና ምርቶች፣ እንዲሁም ከ8.4 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የኢንዱስትሪ ምርቶች በማህበራቱ በኩል ወደ ገበያ እንዲገቡ ተደርጓል።

ይሁን እንጂ አንዳንድ ማህበራት የተቋቋሙበትን "ለሕዝብ መቆም" የሚል መርህ ወደ ጎን በመተው፣ ልክ እንደ ተራ ነጋዴ ከፍተኛ ትርፍ ለማጋበስ ሲሞክሩ፣ እንዲሁም ምርት በመደበቅ እጥረት ሲፈጥሩ መገኘታቸውን ኮሚሽነሩ በግልጽ ተናግረዋል። በእነዚህ ገበያን በማዛባት የችግሩ አካል በሆኑ ማህበራት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑንና አሠራሩን የሚያዘምኑ መመሪያዎችም እየተሻሻሉ መሆኑን አረጋግጠዋል። ማህበራቱ በቂ ምርት ይዘው ከነጋዴዉ በተሻለ ዋጋ ለህብረተሰቡ እንዲያቀርቡ ጥብቅ ክትትል እየተደረገ ይገኛል።

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.