Logo
FBC
ክብር፣ ጽናትና ዘመናዊት - የኢትዮጵያ አየር ኃይል

አዲስ አበባ፣ጳጉሜን 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከተለመደው የባህላዊ ጄት ውጊያ ባሻገር የዘመኑን የዲጂታል መረጃ፣ የቅኝትና የትክክለኛ ጥቃት ቴክኖሎጂዎች ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዛሬም የሰላም ዋስትናና የሉዓላዊነት ማኅተም ሆኖ ዘልቋል።

ነሐሴ 12 ቀን 1921 ዓ.ም የአቪዬሽን ቴክኖሎጂ ወደ ኢትዮጵያ የገባ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል እንደ ተቋም አደረጃጀት ይዞ በይፋ የተመሰረተው ሕዳር 20 ቀን 1928 ዓ.ም ነው።

በወቅቱ ከስዊድን የአቪዬሽን ድርጅቶች ጋር በተደረገ ሁለገብ ትብብር የመጀመሪያው የሰው ኃይል ሥልጠና ተጀምሮ የተለያዩ የጦር አውሮፕላኖችን የታጠቀ ዘመናዊ ኃይል ለመገንባት አስችሎ ነበር።

ይህ ጅምር በደርግ ዘመነ መንግሥት ከሶቪየት ኅብረት ጋር በተደረገው ስልታዊ ወታደራዊ ትብብር ጎልብቷል።

ጀግናው የኢትዮጵያ አየር ኃይል 90 ዓመታትን ባስቆጠረው የምስረታ ታሪኩ በየዘመናቱ ሁሉ የሀገርን ሉዓላዊነት በመጠበቅ አኩሪ ታሪክ ያለው ስመ ገናና ተቋም ነው፡፡

ተቋሙ የኢትዮጵያን የአየር ክልል በጀግንነት ከመጠበቅ ባሻገር በዓለም አቀፍ የሠላም ማስከበር ተልዕኮዎች በመሰማራት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርጎ አውለብልቧል፡፡

ከለውጡ በኋላም የመደመር መንግሥት ባካሄደው አጠቃላይ የመከላከያ ሪፎርም የአየር ኃይሉን አቅም መሠረታዊ በሆነ መንገድ የሚቀይሩ ታላላቅ የዘመናዊነት ሥራዎች ተከናውነዋል።

በዚህም የኢትዮጵያን አየር ኃይል ከተለመደው የባህላዊ ጄት ውጊያ ባሻገር፤ የዘመኑን የዲጂታል መረጃ፣ የቅኝትና የቴክኖሎጂዎች ባለቤት የሆነ የተቀናጀ የአየር መከላከያ መዋቅር አድርጎ ገንብቶታል።

ዛሬ ላይ አየር ኃይሉ በሳተላይትና በዘመናዊ ድሮኖች ሰማይን የሚቆጣጠርበት፣ ያለ አላስፈላጊ ጉዳት ግብን በትክክል የመምታት ልዕልናን የተቀዳጀበትና ከመሬት እስከ ሰማይ የሚዘልቅ ሉዓላዊ የደህንነት ጋሻ የተገነባበት የብቃት ማማ ሆኗል።

ዘመናዊ ተዋጊ አውሮፕላኖችን በመታጠቅ የኢትዮጵያ ብሎም የአፍሪካ ግዙፍ አየር ኃይል በመሆን በተለያዩ ጊዜያት በውጣ ውረዶችና ታሪካዊ ጦርነቶች የአየር ላይ የበላይነቱን፣ የቴክኒክ ብቃቱንና የውጊያ ጽናቱን በግልጽ አስመስክሯል።

የ90 ዓመታት አኩሪ ታሪክና ድል ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ትናንትም ሆነ ዛሬ የሰላም ዋስትናና የሉዓላዊነት ማኅተም ሆኖ ዘልቋል።

በሶስና አለማየሁ

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.