Logo
Getu Temesgen
የስፓይና ቢፊዳ እና ሃይድሮሴፋለስ ታካሚ ህጻናትን ህይወት ለመለወጥ የሚደረግ ጥረት
‎
‎#ethiopia | ​በኢትዮጵያ በአመት ከ14 ሺህ እስከ 50 ሺህ የሚደርሱ ህጻናት የስፓይና ቢፊዳ እና የሃይድሮሴፋለስ የፅንስ አፈጣጠር እክል ገጥሟቸው ይወለዳሉ።
‎
‎ይህንን ከፍተኛ የማህበረሰብ እና የጤና ችግር ለመቅረፍ እንዲሁም የተጠቁ ህጻናትን እና ወላጆቻቸውን ለመደገፍ ሰፊ ህዝባዊ እና መንግስታዊ ንቅናቄ እንደሚያስፈልግ የዘርፉ ባለሙያዎች እና የእንቅስቃሴው መሪዎች ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
‎
‎​የማያ በጎ አድራጎት ድርጅት መስራችና ስራ አስኪያጅ፣ የህግ ባለሙያና ጋዜጠኛ ጠበቃ አበባው አበበ እንደሚገልፁት፣ የስፓይና ቢፊዳ እና ሃይድሮሴፋለስ ችግሮች በዋናነት እናቶች በእርግዝና ወቅት ከሚያጋጥማቸው የቫይታሚን B9 ወይም የፎሊክ አሲድ እጥረት ጋር የተያያዙ ናቸው።
‎
‎ችግሩን ከስሩ ለማስቀረት እና የወደፊት ትውልድን ለመጠበቅ መንግስት የፎሊክ አሲድ እና የቫይታሚን B9 ማበልፀጊያ በምግብ ምርቶች፣ በተለይም በጨው፣ ዘይት እና ዱቄት ላይ አስገዳጅ ሆኖ እንዲካተት ህግ ማውጣቱ ትልቅ የፖሊሲ እርምጃ ነው።
‎
‎ቀደም ሲል የእንግርት (ጎይተር) በሽታን በጨው ውስጥ አዮዲን በመጨመር መከላከል እንደተቻለው ሁሉ፣ አሁንም ጨውን በፎሊክ አሲድ በማበልፀግ የስፓይና ቢፊዳ በሽታን ዘላቂ በሆነ መንገድ መከላከል እንደሚቻል ጠበቃ አበባው አስረድተዋል።
‎
‎​በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የህጻናት የነርቭ ዘንግ ህክምና ክፍል ባለሙያ እና የ"አሊያንስ ፎር ባርዝ ዲፌክትስ" ድርጅት መስራች የሆኑት ዶክተር ነቢያት ተስፋዬ በበኩላቸው፣ ራሳቸው ከስፓይና ቢፊዳ እክል ጋር ተወልደውና በህክምና አልፈው ዛሬ ላይ ሀኪም በመሆን በርካቶችን እያገለገሉ ይገኛሉ።
‎
‎ዶክተር ነቢያት እንደሚሉት፣ የነርቭ ዘንግ እድገት እናት እርጉዝ መሆኗን ሳታውቅ በ28 ቀናት ውስጥ ተጠናቆ ስለሚያልፍ፣ ከእርግዝና በፊት የፎሊክ አሲድ እጥረትን መቅረፍ ወሳኝ ነው። የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጥናት እንደሚያሳየው ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑ በወሊድ እድሜ ላይ ያሉ ሴቶች የፎሊክ አሲድ እጥረት አለባቸው።
‎
‎አሁን ላይ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የጨው፣ የስንዴ እና የዘይት አምራቾች ምርቶቻቸውን ማበልፀግ የጀመሩ ሲሆን፣ በተለይም ከ95 በመቶ በላይ ህብረተሰብ የሚጠቀመውን ጨው በፎሊክ አሲድ የማበልፀግ ስራ በሚቀጥለው አንድ አመት ውስጥ በሰፊው ገበያ ላይ ይውላል።
‎
‎​ከቅድመ መከላከል ጎን ለጎን አሁን በህይወት ያሉ ህጻናት የሚያጋጥሟቸውን ሁለገብ ፈተናዎች መፍታት ሌላው ዋና ትኩረት ሊሆን እንደሚገባ ሁለቱም ባለሙያዎች ያሰምሩበታል።
‎
‎እነዚህ ህጻናት የእንቅስቃሴ እክል እና የሽንትና ሰገራ የመቆጣጠር ችግር ስለሚያጋጥማቸው በትምህርት ቤቶች፣ በህክምና ተቋማት እና በመሰረተ ልማቶች አካባቢ ተገቢውን ድጋፍ አያገኙም። በአሁኑ ወቅት በርካታ ትምህርት ቤቶች ግንዛቤ በማጣታቸው እና ተንከባካቢ ባለሙያ ባለመኖሩ ምክንያት እነዚህን ህጻናት የመቀበል ፍላጎት እንደሌላቸው እናቶች አቤቱታ ያቀርባሉ።
‎
‎​ይህንን ችግር ለመቅረፍ የማያ በጎ አድራጎት ድርጅት ለህጻናቱ የፊዚዮቴራፒ አገልግሎት ያካተተ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመክፈት ህልም እንዳለው ጠበቃ አበባው አበበ ገልፀዋል።
‎
‎ይህ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ህጻናቱ ትምህርት የሚያገኙበት እና እንቅስቃሴያቸውን የሚያሻሽሉበት ብቻ ሳይሆን፣ እናቶችም ልጆቻቸውን በታማኝ ቦታ አስቀምጠው ወደ ስራ በመሰማራት በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ የሚያስችል ነው።
‎
‎በተመሳሳይ መልኩ ዶክተር ነቢያት ተስፋዬ እንደሚያስረዱት፣ ከ"ፐርኪንስ ኤንድ አዘርስ ፋውንዴሽን" እና ከ"ኢፖስ" (EPOS) የመልሶ ማቋቋም ተቋማት ጋር በመተባበር ለህጻናቱ ዘመናዊ የህክምና መሳሪያዎችን፣ ዊልቼሮችን እና ክራንቾችን የማቅረብ ስራ እየተሰራ ይገኛል።
‎
‎​በመጨረሻም፣ ሁለቱም ባለሙያዎች የስፓይና ቢፊዳ እና ሃይድሮሴፋለስ ያለባቸው ህጻናት አዕምሯቸው ሙሉ በሙሉ ጤናማ እና በትምህርታቸው በጣም ጎበዞች መሆናቸውን ገልፀው፣ የትምህርት ሚኒስቴር፣ የጤና ሚኒስቴር፣ መገናኛ ብዙሃን፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና ባለሀብቶች በጋራ በመቆም የህጻናቱን የመማር መብት ሊያስከብሩ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።
‎
‎መገናኛ ብዙሃን ህብረተሰቡን በማንቃት ረገድ የመሪነቱን ሚና እንዲጫወቱና ችግሩ የአንድ ቤተሰብ ብቻ ሳይሆን የሀገር ችግር መሆኑ ተይዞ የተቀናጀ ድጋፍ እንዲደረግ አሳስበዋል።
‎
‎ማያ የበጎ አድራጎት ድርጅት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ፣ ከኢቻ ፉድ ኮምፕሌክስ እና ከክሊን ማቴሪያልስ ጋር በመተባበር በግዮን ሆቴል ባካሄደው መርሀግብር ለ100 አባላቱ የአዲስ አመት የማዕድ ማጋራት መርሐግብር አካሂዷል።
‎
‎ጌትነት ተመስገን
‎📷 ሲሳይ ጉዛይ
‎
‎#spinabifida ​#hydrocephalus
‎​#spinabifidaawareness ​#folicacid
​#foodfortification ​#birthdefects​#healthethiopia ​#mayacharity

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.