Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ስፖርት) ክሪስቲያኖ ሮናልዶና ኒዮኔል ሜሲ በአንድ ቡድን ተሰልፈው ሊጋጠሙ ነው፡፡ ይህ ለእግር ኳስ አፍቃሪዎች ህልም ሊመስል ይችላል፡፡ ሮናልዶና ሜሲ በስፔን ላሊጋ በባርሴሎናና ሪያል ማድሪድ ተሰልፈው ችሎታቸውን አሳይተዋል፡፡ አንዳቸው ከአንዳቸው ለመብለጥ በሚያደርጉት ጥረትም በስፖርት ታሪክ ውስጥ ትልቁ የሚባለው ፉክክር ውስጥ አልፈዋል፡፡ ሜሲ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ በ39 አመቱ ራሱን ከአለም አቀፍ ውድደር አግልሏል፡፡

ሮናልዶም በሚቀጥለው አመት 42 አመት ስለሚሞላው ጫማውን እንደሚሰቅል ይጠበቃል፡፡ እነዚህን ሁለት ኮከቦች በአንድ ቡድን ውስጥ ተሰልፈው ሲጫወቱ ማየት ጊዜው ያለፈበት ይመስላል፡፡ ነገር ግን የቀድሞ የቡድን አጋሮቻቸው ይህ እድል የሚፈጠርበትን አጋጣሚ ፈጥረውላቸዋል፡፡ የአርጀንቲናው ታይሲ ስፖርት እንደዘገበው በመጪው ታህሳስ ወር ካርሎስ ቴቬዝ በታዋቂው ቦካ ጁኒየርስ ስታዲየም የኳስ ጨዋታ ስንብቱን በተመለከተ የኳስ ግጥሚያ ማድረግ አቅዷል፡፡ ለዚህ ግጥሚያ የቦካ ጁኒየርስ ፕሬዝደንት ሁዋን ሮማን ሪኬልሚ ስታዲየሙን እንደፈቀዱለት ዘገባው አስታውቋል፡፡

ምንም እንኳ ጨዋታው የሚካሄድበት እለት እስካሁን ያልተወሰነ ቢሆንም ከዲሴምበር 12 እስከ 20 ባሉት ቀናት እንደሚሆን ግን ተገልጿል፡፡ የቀድሞው የማንችስተር ዩናይትድና የአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን አጥቂው ካርሎስ ቴቬዥ ከቦካ ጁኒየር ሀላፊዎች ጋር ተደጋጋሚ ምክክር እንዳደረገ የጠቀሰው ዘገባው ለጨዋታው ወደ60 ለሚሆኑ ተጨዋቾች ጥሪ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ በዚህ የስንብት ጨዋታ ላይ እንዲገኙ ከሚፈልጋቸውና ጥሪ ካቀረበላቸው መካከል ደግሞ ሮናልዶና ሜሲ በግንባር ቀደምነት ተጠቅሰዋል፡፡

ቴቬዥ ከእነዚህ ሁለት ኮከቦች ጋር የቡድን አጋር ሆኖ የተጫወተ ነው፡፡ ከሜሲ ጋር በአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን ውስጥ አብሮ የተሰለፈ ሲሆን ከሮናልዶ ጋር ደግሞ በማንችስተር ዩናይትድ በርካታ የውድድር ወቅቶችን አሳልፏል፡፡ እንደዘገባው ለሁለቱ ተጨዋቾች ያቀረበላቸው ጥሪ በአንድ ቡድን ውስጥ ተሰልፈው የወዳጅነት ግጥሚያውን እንዲያደርጉ ነው፡፡ ተጨዋቾቹ ጥሪውን ከተቀበሉ በእግርኳስ አለም ህልም የሚመስለው ክስተት እውን ይሆናል፡፡

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.