ጳጉሜ - የጊዜ ድልድይ፣ የትዝታና የተስፋ መገናኛ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአሮጌው ዓመት መጨረሻና በአዲሱ ዓመት መጀመሪያ መካከል ቆማ፣ ያለፈውን በትዝታ እያሰናበተች የሚመጣውን በተስፋ የምትቀበል አንዲት ልዩ ወር አለች፣ እርሷም ኢትዮጵያዊቷ ጳጉሜ ናት።
ጳጉሜ ቀናቷ አምስት ወይም ስድስት ብቻ ቢሆኑም የምትሸከመው ጥልቅ ትርጉም ግን ከቀናት ቁጥር ይረዝማል።
እሷ ያለፈውን ዘመን በአንድ ገጽ ላይ አጠናቃ ለአዲሱ ብሩህ ምዕራፍ መንገድ የምትከፍት፣ የትናንትና የነገ መገናኛ ድልድይ ናት። ወደ ኋላ ለመቅረት ሳይሆን ለጥቂት ጊዜ ቆሞ ይበልጥ ለመፍጠን እና ነገን አርቆ ለማየት የሚደረግ ውብ የመንፈስ ጉዞ ማሳያ ናት፣ ጳጉሜ፡፡
በኢትዮጵያዊያን ህሊና ውስጥ ይህች አጭር ወር የታሪክ ማጠፊያና የይቅርታ ወር ናት። ያለፈውን ዓመት ድካም፣ ጭንቅና ቅሬታ አራግፋ እና አጽድታ፣ በአዲስ መንፈስ ለአዲሱ ዘመን ንጹህ ልብና አዲስ መንፈስ ታዘጋጃለች።
በጳጉሜ ሰዎች ከተጣሉት ጋር የሚታረቁበት፣ የፈጣሪን ምህረት በጸሎት የሚያስቡበት ቅዱስ ጊዜ በመሆኑ በማህበረሰባችን ዘንድ ልዩ የክብር ስፍራ አላት።
ይህ የመታደስ መንፈስ በተግባርም ይገለጣል። ጳጉሜ ሲመጣ ህፃናት፣ ወጣቶችና አዋቂዎች ጎህ ሳይቀድ ተነስተው ወደ ወንዝ ያመራሉ። በወሩ የሚዘንበው ዝናብና የሚፈሰው ውሃ ፈውስና በረከት አለው ተብሎ ስለሚታመን፣ ያለፈው ዓመት ደካማነትና ህመም በሙሉ ታጥቦ ይሄዳል ተብሎ ይታመናል።
በየቤቱም አዲስ አመትን ለመቀበል የሚደረገው ጉድጉድም በነዚህ ቀናት ነው የሚካሄደው፡፡
እናቶች የቤታቸውን ውበት እያደሱ ለአዲሱ ዓመት የእንቁጣጣሽ በዓል ሲሰናዱ፣ ህፃናት በየደጃፉ በቅኔና በጨዋታ ድምፃቸው መንደሩን ያደምቁታል። ይህም ልዩ የመታደስ የሽግግር መንፈስ እና የበዓል ድባብ ያላብሳል፡፡
ጎረቤት ከጎረቤቱ ጋር የሚጠያየቅበት፣ አረጋውያን የሚጎበኙበትና ያለው ከሌለው ጋር ተካፍሎ የሚበላበት ይህ ወቅት የኢትዮጵያዊነትን የመደጋገፍና የፍቅር እሴት በጉልህ ያሳያል።
በዚህም ጳጉሜ አንድ ትልቅ እውነት ታስተምረናለች፡፡ ይህም የአንድ ነገር መጨረሻ የሕይወት መጨረሻ ሳይሆን የአዲስ ጅምር መነሻ ሊሆን እንደሚችል ነው ።
ያለፈውን አስተውለን፣ ከስህተታችን ተምረን፣ ወደ አዲሱ ዓመት በተስፋ እንድንሻገር ጳጉሜ የተስፋ ድልድይ ሆና ታገለግላለች።
በአመለወርቅ ደምሰው

1 month ago