Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) በኦሮሚያ ክልል፣ ምዕራብ አርሲ ዞን ቆሬ ወረዳ፣ የትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች ለግዳጅ ወታደራዊ አገልግሎት እንዲውሉ በመደረጉ ምክንያት የአካባቢው ማህበረሰብ ለከፍተኛ እንግልት መዳረጉ ተገለጸ።

በአካባቢው ካለው አስገዳጅ ሁኔታ አኳያ አብዛኛዎቹ መኪኖች ሲያዙ የተረፉት ደግሞ ሸሽተው በመደበቃቸው በወረዳው የትራንስፖርት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ቆሟል። በመሆኑም አማራጭ ያጣው ማህበረሰብ፣ በተለይም ነፍሰጡር እናቶች እና አረጋውያን በዝናብ ውስጥ ክፍት የጭነት (አይሱዙ) መኪናዎች ላይ ታጭቀው ከቆሬ ወደ ሻሸመኔ ከተማ ለመጓዝ ተገደዋል።

ይህንን አሳዛኝ ትዕይንት ይበልጥ ልብ ሰባሪ የሚያደርገው የአረጋውያኑ ምላሽ ነው። "በዚህ ዝናብና ቅዝቃዜ ለምን እንዲህ ተንገላትችሁ ትጓዛላችሁ?" ተብለው ሲጠየቁ፤ "ለዓመታት ደክመን ያስተማርናቸው ልጆቻችን ዛሬ ከኮሌጅ ስለሚመረቁ፣ ያንን የምረቃ ደስታ ለመድረስ ብለን ነው" ሲሉ ምላሽ መስጠታቸው ተዘግቧል።

ይህ ድርጊት አሳፋሪ መሆኑን የሚገልጸው የመረጃው ምንጭ፤ አካላቱ "ለህዝብ ቆመናል" እያሉ ሰፊውን ማህበረሰብ እንዲህ ላለ ሰቆቃ መዳረጋቸው እጅግ አሳዛኝ እና አንጀት አቃጣይ መሆኑን በጽኑ ይተቻል።

የቆሬ ወረዳ ህዝብ ቀድሞውንም የተስተካከለ የመንገድ መሠረተ ልማት የሌለው መሆኑ ይታወቃል። ነገር ግን በፈራረሰው መንገድ ላይ እየተጓዙ ህዝቡን በችግሩ ጊዜ ሲያገለግሉ የነበሩት ጥቂት ተሽከርካሪዎችም "በግዳጅ ስም" ስራ እንዲያቆሙ መደረጉ፣ ማህበረሰቡን ለከፋ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ዳርጎታል።

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.