የፒያሳዎቹ ወግ፡ ከዘመናዊነት ማዕበል እስከ የኢኮኖሚው ሞተር
«ፒያሳ» የሚለው ቃል በኢትዮጵያ የከተማ ሥነ ሕንጻ እና ማኅበራዊ ታሪክ ውስጥ ከቀላል የስፍራ መጠሪያነት እጅግ የራቀ ትርጉም አለው።
ፒያሳዎች የከተሞች የልብ ትርታ፣ የባህል መስተጋብር፣ የንግድ ማዕከል እና የዘመን መሻገሪያ ሕያው ድልድዮች ናቸው።
ታዋቂው አሜሪካዊ የታሪክና የከተማ ባህል ተቺ ሉዊስ ሙምፎርድ ከተማን ሲገልጻት፤ ከተማ በተፈጥሮ ውስጥ እንዳለ ዋሻ ወይም የጉንዳን ክምር ያለ እውነታ ብቻ ሳትሆን፤ በተመሳሳይ ጊዜ የሰው ልጅ የንቃተ-ህሊና የጥበብ ሥራ ጭምር መሆኗን ያነሳል።
አእምሮ በከተማ ውስጥ ቅርፅ ይይዛል፤ በምላሹም የከተማ ቅርጾች የአንድን ማኅበረሰብ አእምሮ ይቀርጻሉ። ሙምፎርድ እንደሚሞግተው ከተሞች የሰውን ልጅ ሥልጣኔና ማኅበራዊ ትስስር የሚመግቡ ሕያው የኪነ-ጥበብ መድረኮች ናቸው።
ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ ከተሞች በከፍተኛ ፍጥነት እየተተገበረ ባለው ሀገራዊ የኮሪደር ልማት እና የከተማ ዝመና ፕሮጀክት ምክንያት የሀገሪቱ አንጋፋ የሆኑት የአዲስ አበባ እና የሀዋሳ ፒያሳ ሰፈሮች የትናንት የጥበብና የማኅበራዊ ትስስር ትዝታቸውን ከዛሬው ዘመናዊ መልክ፣ ምቹ የኑሮ ዘይቤ እና ግዙፍ የኢኮኖሚ አቅም ጋር እያዋሃዱ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እየጻፉ ይገኛሉ።
የአዲስ አበባ ፒያሳ፡ ከትዝታ ማዕከልነት ወደ ግዙፍ የኢኮኖሚና የግብይት እምብርት..
የአዲስ አበባ ፒያሳ የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ታሪክ መናገሻ ናት። በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን ተቆርቁራ፣ በጣሊያን ወረራ ወቅት የተለየ የስነ-ሕንጻ ገጽታን የተላበሰችው ይህች ሰፈር፤ በሲኒማ ቤቶች፣ በጥንታውያን የወርቅ ቤቶች እና በስፖርት ካፌዎች የምትታወቅ የከተማዋ «ነፍስ» ናት።
የትናንቷ ፒያሳ የፍቅርና የውበት ማዕከል፣ ግብይት የሚደራባትና በሁሉ ተወዳጅ ሰፈር ነበረች። አሁን ግን የኮሪደር ልማቱን ተከትላ ፒያሳ ፊቷን ሙሉ በሙሉ ወደላቀ የከተሜነት ደረጃ ተቀይራለች።
ዛሬ ላይ ፒያሳ የመንገድ ማሳለጫ ብቻ ሳትሆን፣ ግዙፍ የኢኮኖሚና የሥራ ዕድል ፈጠራ ሞተር ሆናለች።
በግርማ ሞገስ የቆመው የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ አዲሱ የዓድዋ ገበያ ማዕከል እና ዘመናዊው የትራንስፖርት ተርሚናል አካባቢውን ወደ ከፍተኛ የንግድና የኢንቨስትመንት ማዕከልነት አሸጋግረውታል።
እነዚህ ዘመናዊ የግብይት ማዕከላት በሺዎች ለሚቆጠሩ ወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠራቸውም ባሻገር፣ ሸማቹ ማኅበረሰብ በአንድ ማዕከል የተሟላ አገልግሎት እንዲያገኝ አስችለዋል።
ቀድሞ የነበረውን መጨናነቅ በማስቀረት፤ ሰፋፊና ደረጃቸውን የጠበቁ የእግር ጉዞ መንገዶች፣ ደኅንነታቸው የተረጋገጠ የብስክሌት መስመሮች፣ እንዲሁም ነዋሪው አየር የሚቀበልባቸው አረንጓዴ ፓርኮች የፒያሳን የድሮ ድባብ ወደ ዘመናዊ የቅንጦት እና የዕረፍት መዳረሻነት ቀይረውታል።
የአካባቢው ነዋሪዎችም የድሮዋን ፒያሳ ትዝታ እያደሱ፣ ዛሬ ላይ የሚታየው ንጽህና፣ ውበትና ሥርዓት ያለው የንግድ እንቅስቃሴ ለትውልድ የምትመች ዘመናዊ ከተማን ማስረከቡን ይመሰክራሉ።
የሀዋሳ ፒያሳ፡ የጥበበኞች ማረፊያ እና የስማርት ሲቲ ጉዞ
ከአዲስ አበባ ወደ ደቡብ ስናመራ የምናገኛት የሀዋሳ ፒያሳ ደግሞ የራሷ የሆነ የተለየ የታሪክ ውበትና አዲስ የዝመና ጉዞ አላት።
በ1950ዎቹ የተመሠረተችው ሀዋሳ፣ ከሐይቁ በሚነፍሰው ቀዝቃዛ አየር፣ በብስክሌት ተጠቃሚዎቿ፣ በሰላማዊ ማኅበራዊ ኑሮዋ እና በቡና ባህሏ ትታወቃለች። ይህች ከተማ በታዋቂ ሀገር በቀል ከዋክብት እይታ ስትገለጽ ይበልጥ ደማቅ ትሆናለች።
ለምሳሌ ልዑል ራስ መንገሻ ስዩም የከተማዋን እድገት በምድራዊት ገነት መስለው፣ "ሀዋሳ ለእኔ ጥሩ አትክልተኛ እንዳገኘው አይነት የአትክልት ሥፍራ ናት፤ ኃላፊነት የወሰደ፤ በተገቢው መልኩ ውሃ የሚያጠጣ እና የሚኮተኩት አካል ያላት ምርጥ ከተማ"ሲሉ አሞግሰዋታል።
የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ በበኩላቸው "የትም ብትሆን መንፈስህን ታድሳለህ... የተሸላሚነት ሥራዎቼ ንድፈ ሃሳብ የተገኙት በዚህች ከተማ ለማረፍ ስመጣ ነው" በማለት የሀዋሳን የፈጠራ ማነቃቂያነት መስክረዋል።
ዛሬ ላይ ይህችው የሀዋሳ ፒያሳ፣ በከተማዋ እየተተገበረ ባለው የኮሪደር እና የመሠረተ ልማት ግንባታ አማካኝነት ወደ ስማርት ሲቲ እየተለወጠች ትገኛለች።
የድሮዎቹ ዝቅተኛ ሕንጻዎች ቦታቸውን ለባለብዙ ፎቅ ሆቴሎች፣ ለዓለም አቀፍ ደረጃ ላላቸው የገበያ አዳራሾች እና ለዘመናዊ የንግድ ኮምፕሌክሶች ለቀዋል።
ይህ የንግድ መሠረተ ልማት መስፋፋት ሀዋሳን የሲዳማ ክልል ዋነኛ የቱሪዝምና የኮንፈረንስ ማዕከል ከማድረጉም በላይ፤ የአካባቢውን ኢኮኖሚ በማነቃቃት ለበርካቶች የሥራ ዕድል ፈጥሯል።
የጎዳናዎቹ መብራት፣ ሰፋፊ የእግረኛ መንገዶች እና አረንጓዴ ልማት ነዋሪውም ሆነ ጎብኚው ያለምንም ስጋት ሌሊትና ቀን እንዲንቀሳቀስና እንዲገበያይ ምቹ ሁኔታን ፈጥረዋል።
ከአዲስ አበባ እና ከሀዋሳ የፒያሳ ዝመናዎች ጀርባ አንድ ትልቅ ሀገራዊ የከተማ ፕላን ፍልስፍና አለ። ይኸውም «የመደመር መንግሥት» በተሰኘው መጽሐፍ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው፣ መገንባት የምንፈልጋቸው የአዲሱ ዘመን ከተሞች አካታችነትን ማዕዘን ድንጋይ ያደረጉ መሆን አለባቸው።
በነባር ከተሞች እድሳትም ሆነ አዳዲሶችን ከመገንባት አኳያ ለአይበገሬነት ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገሩ ሆነው መታቀድና የከተማ ደኖችን ጨምሮ አረንጓዴ መሠረተ ልማቶችን ማካተት አለባቸው ይላል መጽሐፉ።
በመሆኑም፤ ዛሬ ላይ በሁለቱ ፒያሳዎች የምናየው የጎዳና ማስፋፋት፣ የፓርኮች ግንባታ እና የመሠረተ ልማት እድሳት እንዲሁ ለውበት ብቻ የተሠራ ሳይሆን፣ ከተሞቹ ሁኔታዎችን በቀላሉ ተላማጅ የሆነ የከተማ አወቃቀር እንዲኖራቸው ታስቦ ነው።
ይህ ተላማጅ አወቃቀር የንግድ እንቅስቃሴን በማሳለጥ፣ ኢንቨስትመንትን በመሳብ እና የስነ ሕዝብ ለውጦችን በቀላሉ በማስተናገድ ከተሞች ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ የኢኮኖሚ ዋልታ ሆነው እንዲያድጉ ያስችላል።
አዲስ አበባ እና ሀዋሳ ዛሬ ላይ የሚያወጉን እውነት ቢኖር፤ የትናንቱ ጠባብ መንገድ እና ያረጁ ቤቶች ለአረንጓዴ አካባቢዎች፣ ለሰው ልጅ ምቹ ለሆኑ መንገዶች፣ ለዘመናዊ የግብይት ማዕከላት እና ለአየር ንብረት የማይበገሩ መሠረተ-ልማቶች ቦታቸውን መልቀቃቸው የማይቀሬ የዕድገት እና የስልጣኔ ጉዞ መሆኑን ነው።
የኢትዮጵያ ፒያሳዎች ትናንትም የፍቅር፣ የኪነ-ጥበብና የታሪክ መድረክ ነበሩ፤ ዛሬም የኢኮኖሚ ሞተር በመሆን፣ አካታችነትንና አይበገሬነትን መሠረት አድርገው በዘመናዊነት አሸብርቀው የነገዋን ውብ ኢትዮጵያ የሚከትቡ የሥልጣኔ አውራ ጎዳናዎች ሆነው ቀጥለዋል።
በኃይለኢየሱስ መኮንን

1 month ago